ላለፉት ሰድስት ተከታታይ ዓመታት ኢትዮጵያ ባለ ሁለት አሃዝ ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት አስመዝግባለች፡፡ ይህም የተቻለው የራሷ የሆነ ወጥ እና ተጨባጭ የሆነ ምጣኔ ሃብታዊ እና ማህበራዊ ሂደቶችን መሰረት ያደረገ የምጣኔ ሃብት ፍኖተ-ካርታ አዘጋጅታ በስራ ላይ በማዋልዋ ነው፡፡ የአብዛኛው የሃገሪቱ ህዝብ ኑሮ በግብርና ላይ የተመሰረተ እንደመሆኑ መጠን ብሔራዊ የምጣኔ ሃብት ዕቅዱም ለግብርና ትልቅ ትኩረት መስጠት እና ግብርና መርም ሊሆን ይገባል፡፡ ስለዚም የሃገሪቱ ብሔራዊ የምጣኔ ሃብት ፍኖተ-ካርታ ግብርና መር የኢንዱስትሪ ልማት ነው፡፡
በደምሳሳው የሃገሪቱ ብሔራዊ የልማት ዕቅድ ዋና ዋና ግቦች፡- ድህነትን ከስሩ ማጥፋት፣ የሚሊኒየሙን የልማት ግቦች ለማሳካት የተፋጠነ እና ዘላቂነት ያለው ድህነትን የማጥፋት ዕቅድን የያዙ ዕቅዶችን እንደ ዋነኛ መሳሪያ መጠቀም እንዲሁም የግሉን ዘርፍ ማሳደግ እና የሚሊንየሙን የልማት ግቦች ሃብትን በሚገባ መጠቀም ናቸው፡፡
የተፋጠነ እና ዘላቂነት ያለው ድህነትን የማጥፋት ዕቅድ አጠቃላይ ዓላማ
የዕቅዱ ዋነኛ ዓላማ የተፋጠነ እና ዘላቂነት ያለው እና ህዝባዊ የምጣኔ ሀብት እድገትን አቅጣጫ ማስያዝ ከዚህም በተጨማሪ የሚሊንየሙ የልማት ግቦች እንዲሳኩ ማድረግ ነው፡፡ ይህም ኢትዮጵያ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሃገሮች ተርታ ለመግባት ያላትን ራዕይ እውን እንዲሆን ያግዛል፡፡