Back

በመንግስት የፋይናንስ አስተዳደርን አስመልክቶ ምክክር ተካሄደ

በመንግስት የፋይናንስ አስተዳደርን አስመልክቶ ምክክር ተካሄደ

 

የመንግስት ፋይናንስ በታለመለት ዓላማ እንዲተገበር እንዲሁም የመንግስት ውስን ሀብት በቁጠባና ውጤታማ በሆነ መልኩ ስራ ላይ እንዲውል ለማስቻል ከመንግስት መ/ቤቶች ከፍተኛ አመራሮች ጋር በገንዘብ ሚኒስቴር ምክክር ተካሄደ፡፡

 

የፌዴራል መንግስት የአስፈፃሚ አካላትን ስልጣንና ተግባር ለመወሰን በአዋጅ ቁጥር 1097/2011 መሰረት በጥቅምት ወር 2011 ዓ.ም. አዲስ የአስፈፃሚ አካላት አደረጃጀትን ተከትሎ አዳዲስ አመራሮች በመመደባቸው የመንግስት ሀብት በተገቢው መልኩ ጥቅም ላይ እንዲውል ግንዛቤ ለማስጨበጥ ውይይቱ እንዳስፈለገ የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ኢዮብ ተካልኝ በውይይቱ መክፈቻ ገልፀዋል፡፡

ጥር 22 ቀን 2011 ዓ.ም. ለግማሽ ቀን በተካሄደው የውይይት መድረክ ላይ በፊሲካል ፖሊሲ አቅጣጫዎች፣ በመንግስት ፋይናንስ፣ በግዥና ንብረት አስተዳደር፣ በመንግስት ፋይናንስ ቁጥጥር እንዲሁም የመንግስት እና የግል አጋርነት በተሰኙት ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ገለፃ ተደርጓል፡፡ አመራሮች በየጊዜው ሊቀያየሩ ስለሚችሉ ውይይቱ ተከተታይነት ቢኖረው የመንግስት ሀብትን በአግባቡ የመጠቀም ባህልን ለማዳበር እንደሚረዳ ተሳታፊዎች አስተያየት ሰጥተዋል፡፡       

 

በውይይት መድረኩ ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ ኮሚሽነሮችና ም/ኮሚሽነሮች፣ ዋና ዳይሬክተሮችና ም/ዋና ዳይሬክተሮች እንዲሁም ሌሎች የመንግስት አመራሮች ተካፍለዋል፡፡ በቀጣይም ተመሳሳይ ውይይት ከዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶችና ከዩኒቨርሲቲ የፋይናንስና በጀት ኃላፊዎች ጋር ይካሄዳል፡፡

 

 

 


News Archive News Archive