የክቡር የገንዘብ ሚኒሴቴር  ክቡር አቶ  አህመድ ሽዴ መልዕክት

እንኳን ወደ ገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ድረገፅ በሰላም መጣችሁ፡፡

ሚኒስቴር መ/ቤቱ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ መንግስትን የበጀት፣ የሒሳብ አያያዝ፣ የክፍያና የውስጥ ኦዲት ሥርዓት መዘርጋት፣ በሥራ ላይ መዋሉን መከታተል፣ የፌዴራል መንግስቱን በጀት ማዘጋጀት፣ በተፈቀደው በጀት መሠረት ክፍያ መፈፀም፣ የኢኮኖሚ ትብብርና የፊሲካል ፖሊሲዎችን ማመንጨት፣ የውጭ ዕርዳታና ብድር ማሰባሰብ፣ ከተለያዩ መንግስታት ጋር የሚደረገውን የሁለትዮሽ ኢኮኖሚ ትብብር እንዲሁም የኢኮኖሚ ትስስር ለመፍጠር ከተቋቋሙ ዓለም አቀፍና አህጉራዊ ድርጅቶች ጋር የሚደረገውን ግንኙነት መምራት፣ በአዋጅ ከተሰጡት ስልጣንና ኃላፊነቶች ዋነኞቹ ናቸው፡፡

በመንግስት የተነደፈ የልማት ፕሮግራሞች ለማሳካትና ድህነትን ለመቀነስ እንዲሁም የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ የሚቻለው የመንግስት ፋይናንስ አስተዳደር ውጤታማ ሲሆን ነው፡፡ ይኸውም ውጤታማ የሆነ የፕሮግራም በጀት መተግበር፣ ዘመናዊ የጥሬ ገንዘብ ክፍያ መዘርጋት፣ ዘመናዊ የመንግስት የሂሳብ አያያዝና የሪፖርት አቀራረብ መተግበር፣ የመንግስትን ገንዘብ ከብክነት ለመከላከል የሚያስችል ጠንካራ የውስጥ ኦዲት ማቋቋምና መተግበር፣ የፋይናንስ ሥራውን የሚደግፍ ዘመናዊ የመረጃ ሥርዓት መዘርጋት እና አሰራሩን ማጠናከር ቅድሚያ የሚሰጣቸው ቁልፍ ሥራዎች ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ፊስካል ፖሊሲም የልማታዊ መንግስት ዓላማዎችን ለማስፈፀም በመንግስት ገቢ፣ ወጪ፣ ብድርና የውጭ እርዳታ አስተዳደር አማካኝነት ሥራ ላይ የሚውል ሌላው ቁልፍ መሣርያ ነው፡፡ በመሆኑም የመንግስትን ሀብት በብቃት ለማስተዳደር አቅም ያለው ጠንካራ እና ውጤታማ ተቋም ለመሆን እንጥራለን፡፡

ኢኮኖሚያችን ከ2003-2007 ባሉት ዓመታት በየዓመቱ በአማካይ በ10.1 በመቶ ዕድገት አስመዝግቧል፡፡ ይህም በዕቅድ  ከተቀመጠው ዓመታዊ አማካይ ግብ አንጻር የተሳካ አፈጻጸም እንደነበር አመላካች ነው፡፡ ባለፉት ዓመታት የተመዘገበው  ዕድገት  ዓመታዊ  አማካይ  የዜጎች  የነፍስ-ወከፍ ገቢ በ2002 ከነበረበት 377 የአሜሪካን  ዶላር በ2008 መጨረሻ ወደ  794  የአሜሪካን ዶላር እንዲያድግ አድርጓል፡፡  እንዱሁም  የኢኮኖሚ  ዕድገቱ  ህብረተሰቡን በሰፊው  ያሳተፈና በሁለም  የኢኮኖሚ  ዘርፎች  የተመዘገበ  (Inclusive growth)  በመሆኑ  የዜጎች  የድህነት  መጠን እንዲቀንስ አድርጓል፡፡

ሀገራችን የተለመችውን በ2025 ዓ.ም. መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገሮች ተርታ የመሰለፍ ራዕይ እውን የማድረግ ጉዞ ረጅምና ፈታኝ ቢሆንም የተቀመጡትን ግቦች ለማሳካት እንቅፋት የሆነብንን የፋይናንስ እና የሰለጠነ የሰው ኃይል ክፍተት ለመቅረፍ ከልማት አጋሮች የሚገኝ እርዳታ አንዱ አማራጭ ነው፡፡ ሀገሪቱ ቅድሚያ በምትሰጣቸው ዘርፎች እንደ ግብርና፣ ውሃ፣ ኢነርጂ፣ መሠረተ ልማት የመሳሰሉትን በብቃት ለመተግበር በተለይም ሀገራችን ኢትዮጵያን የምስራቅ አፍሪካ የኤሌትሪክ ኃይል ማመንጫ ማዕከል ለማድረግ ከውጭ ትብብር የሚገኙ ድጋፎች ጠቃሚነታቸው የጎላ ነው፡፡ በመሆኑም በትብብር የተገኘ ሀብትን በአግባቡ ለታለመለት ግብ በማዋል ራዕያችንን ማሳካት ከእያንዳንዱ ባለ ድርሻ አካል የሚጠበቅ ግዴታ ነው፡፡  

ኢኮኖሚያዊ ስኬቶቻችን እውን ሊሆኑ የቻሉትም በመንግስትና በህዝብ የጠነከረ ግንኙነት እንዲሁም ከልማት አጋራት ጋር ባለን የዳበረ ወዳጅነት ነው፡፡ በዚህም በሀገር ደረጃ ያለ የአመራር ጥበብ ለዘለቀ የኢኮኖሚ ትብብር በር ከፋች መሆኑን ተረድተናል፡፡ ጠንካራ አጋርነት በስኬት ሊዘልቅ የሚችለውም እርዳታ ተቀባይ ሀገሮች ለልማት ቅድሚያ የሚሰጧቸው  ዘርፎችን ከግምት ያስገባ ጠንካራ እና ሁሉን አቀፍ የልማት ትብብር ፖሊሲና ማዕቀፍ ሲኖር ብቻ ነው፡፡

ክቡርአቶ አህመድ ሽዴ

ገንዘብ ሚኒስትር