የክቡር የገንዘብ ሚኒሴቴር  ኤታ የአቶ አድማሱ ነበበ መልዕክት

የመንግሥት አስፈጻሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር      916/2008 መሰረት የገንዘብ ሚኒስቴር ከተሰጡት ተግባራትና ኃላፊነቶች መካከል አንዱ የውጭ ሀብት ማሰባሰብና ማስተዳደር ነው፡፡

የውጭ ሀብት ግኝትና አስተዳደርን የሚመራው የኢኮኖሚ ትብብር ዘርፍ ተግባራትና ኃላፊነቶቹን ለመወጣት በሚችልበት አግባብ በሚኒስትር ደኤታ እና በስድስት ዳይሬክቶሬቶች ተደራጅቶ ሥራውን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡

 

በዘርፉ ከሚከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት መካከል ከበይነ-መንግሥታዊ (Multilateral) ምንጮች ማለትም የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት፣ የአውሮፓ ህብረት፣ የተባበሩት መንግሥታት እና የአየር ንበረት ለውጥ ተቋማት እና ከ20 በላይ የልማት አጋር መንግሥታት (Bilateral) ጋር የኢኮኖሚ አጋርነትን በመፍጠርና በየጊዜውም እንዲጎለብት በማድረግ አገሪቱ ለነደፈቻቸው የአጭርና የመካከለኛ ጊዜ የልማት ፕሮግራሞች ማስፈጸሚያ የሚውል የውጭ ሀብት (የፋይናንስና የቴክኒክ ድጋፍ) ማሰባሰብና የመንግሥትን የበጀት አስተዳደርና የግዢ ሥርዓቶችን ተከትሎ ሥራ ላይ እንዲውል ማድረግ፣ የተገኘው ሀብት ሕጉ በሚፈቅደው የፕሮግራም ስምምነቶች መሰረት በአግባቡ ሥራ ላይ መዋሉን መከታተል፣ ከአለም አቀፍ ሬቲንግ ኤጀንሲዎችና ተቋማዊ ኢንቨስተሮች ጋር የሚደረገውን ግንኙነት ማስተባበር፣ በማደግ ላይ ከሚገኙ አገሮች ጋር በደቡብ ደቡብ ትብብር የጋራ ትብብርን ማጠናከርና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንዲሁም ጤናማ የብድር አስተዳደርን ማረጋገጥና በዚህም ረገድ ግልጽነትንና ተጠያቂነትን ማስፈን የሚሉት ተጠቃሾች ናቸው፡፡

 

 

ከዚህ ሌላ የመንግሥትና የግሉን ዘርፍ አጋርነት (Public Private Partnership) ተቋማዊ በማድረግ ከዚህ ዘርፍ ተጨማሪ ሙአለ-ንዋይ ለመሳብ የፖሊሲና የሕግ ማእቀፍ ሥራዎች ተጠናቀው የአደረጃጀት ሥራዎች እና የፕሮጄክቶች መረጣ ተግባራት በመከናወን ላይ ይገኛሉ፡፡ 

በቀጣይነትም አሰራራችንን በማሻሻል፣ ተነሳሽነታችንን በማሳደግ እንዲሁም በፕሮጄክቶች አፈጻጸም የቅርብ ድጋፍና ክትትል በማድረግ ተጨማሪ የውጭ ሀብት እንዲመጣ በማድረግ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱን እና የተባበሩት መንግሥታት ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካትና ቀጣይና ዘላቂ ልማት እና ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዕድገት በማረጋገጥ የሕዝባችንን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት ጉልህ ድርሻ ለማበርከት እንተጋለን፡፡

በገንዘብ ሚኒስቴር የፊሲካል ፖሊሲ እና ፐብሊክ ፋይናንስ ዘረፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር እዮብ ተካልኝ መልዕክት

 

ለገንዘብ ሚኒስቴር ከተሰጡት የሥራ ኃላፊነቶች መካከል አንዱ የመንግሥት ፋይናንስ አስተዳደር ነው፡፡ ዘርፉ የሀገሪቱን የፊሲካልና የታክስ ፖሊሲ በመቅረጽና አፈጻጸሙን በመከታተል፣ ለልማት አስፈላጊ የሆነውን በጀት በመመደብ፣ ለፌዴራል ፈጻሚ አካላትና ለክልል የበጀት ድጋፍ ገንዘብ በማስተላለፍና ወጪን በአግባቡ በማስተዳደር፣ የመሠረታዊ አገልግሎቶች በስፋት፣ በጥራትና ፍትሃዊነትን ግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ ያስተገብራል፡፡

 

የፊሲካልና የታክስ ፖሊሲው የኢኮኖሚውን አቅጣጫ ከመምራት ባሻገር የኢኮኖሚ ዕድገትን ግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ የሀገሪቱን ልማት ለመደገፍ የሚያሰፈልገውን የፋይናንስ አቅም ለማሳደግ የገቢ መሠረትን ማስፋትና ማጐልበት፣ በተለይም ከሀገር ውስጥ ምንጮች (Domestic Revenue) የሚገኘው ገቢ ለማሳደግ ጠንካራ የገቢ አሰባሰብ ሥርዓት እንዲዘረጋ ያደርጋል፡፡

 

የመንግሥት ወጪ ፖሊሲ ትኩረት የሀገሪቱን ውስን ሀብት ዕድገትን በሚያፋጥኑና ድህነትን በሚቀንሱ የልማት ዘርፎች እና የካፒታል ክምችት በሚያሳድጉ የካፒታል ኢንቨስትመንቶች ላይ እንዲውል ውጤታማና ፍትሃዊ ድልድል ማድረግ ነው፡፡ በመሆኑም የበጀት ምደባው በካፒታል ኢንቨስትመንት እና እንደ ትምህርት፣ ጤና፣ ግብርናና ምግብ ዋስትና፣ ውሀ እና  መንገድ ለመሳሰሉት ድህነት ተኮር ዘርፎች ልዩ ትኩረት ይሰጣል፡፡

 

በፌዴራል፣ በክልሎችና በከተማ አስተዳደሮች፣ በዞንና በወረዳ ደረጃዎች በሚገኙ የልማት ፕሮግራምና ፕሮጀክት ፈጻሚ የመንግሥት ተቋማት የፋይናንስ ዲሲፕሊን እንዲከበር በማድረግ የሀገር ሀብት ለሀገር ግንባታ እንዲውል ጠንክሮ ይሰራል፡፡