በኢንቨስትመንት ቀረጥና ታክስ ማበረታቻ መመሪያ ረቂቅ ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ ተካሄደ
Published: Oct. 8, 2026
መሰከረም 28/2019 ዓ.ም- የገንዘብ ሚኒስቴር በኢንቨስትመንት ቀረጥ እና ታክስ ማበረታቻዎች አፈጻጸም ላይ የተዘጋጀውን አዲስ የመመሪያ ረቂቅ አስመልክቶ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ አካሄደ።
የተዘጋጀው መመሪያ በኢንቨስትመንት ማበረታቻ ደንብ ቁጥር 586/2018 የተሰጡ ማበረታቻዎችን በብቃት ለመተግበር፣ የመንግስትን የፊስካል ጥቅም የሚያስጠብቅና ግልጽ አሰራር ለመዘርጋት እንዲሁም ለልማት የሚሰጡ ማበረታቻዎችን በአንድ ቋት ለማጠቃለል ያለመ እንደሆነ ተገልጻል።
የገንዘብ ሚኒስቴር የህግ ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ አቶ ተወዳጅ መሀመድ እንደተናገሩት በደንብ ቁጥር 586/2018 የተደነገጉትን የኢንቨስትመንት ማበረታቻዎች በአግባቡና በብቃት ለመተግበር አዲስ የመመሪያ ረቂቅ ተዘጋጅቷል።
ኃላፊው በምክክር መድረኩ ላይ እንደገለጹት የመመሪያው ዋነኛ አላማ መንግስት ለባለሃብቶች በሚሰጠው ማበረታቻ ምክንያት የሚያጣው ገቢ ባለሃብቶቹ ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት ከሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ጋር የተመጣጠነ እንዲሆን ማድረግ፣ የመንግስትን የፊስካል ጥቅም የሚያስጠብቅና ግልጽነት ያለው አሰራር መዘርጋት ነው።
ረቂቅ መምሪያው የቁጥጥር ስርዓትና የተጠያቂነት አሰራር ከመዘርጋት ባለፈ ባለሃብቶች ማበረታቻውን ከመጠቀማቸው በፊት የአፈጻጸም ስምምነት የሚፈርሙ ሲሆን፣ ለእያንዳንዱ ፕሮጀክት የተለየ የሂሳብ መዝገብ የመያዝ፣ አመታዊ ሪፖርት የማቅረብና ከቀረጥ ነጻ የገባውን እቃ ለታለመለት አላማ ብቻ የመጠቀም ግዴታ ተጥሎባቸዋል። ግዴታቸውን ባልተወጡና ጥፋት በፈጸሙ አካላት ላይም እርምጃ ይወሰዳል ሲል ጠቅሷል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት በገንዘብ ሚኒስቴር የታክስ ፖሊሲ መምሪያ ኃላፊ አቶ ሙላይ ወልዱ እንደገለጹት የቀረበው የፖሊሲ ማሻሻያ ሀገራችን ከደረሰችበት ወቅታዊ ሁኔታና ከዓለም አቀፍ አሰራሮች ጋር የተጣጣመ ነው
አቶ ሙላይ አክለውም የማሻሻያው ዋነኛ ዓላማ ውጤታማ ያልሆኑ የታክስ ማበረታቻዎችን በማስቀረት የታክስ ወጪን መቀነስ፣ የመንግስት ገቢን ማሻሻል እና የሚሰበሰበውን ገቢ ለመሰረተ ልማት በማዋል ለኢንቨስትመንት ይበልጥ ምቹ አካባቢን መፍጠር ነው ብለዋል።