ለልማት አጋሮች በትግራይ ክልል ስለተካሄደው የህግ ማስከበርና መልሶ ማቋቋም እንቅስቃሴ ማብራሪያ ተሰጠ
በኢትዮጵያ ለሚገኙ የልማት አጋሮች ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት በትግራይ ክልል ህግ ለማስከበር ከተወሰደው እርምጃ በኋላ የክልሉን ሰላም ወደ ነበረበት ለመመለስ ስለተደረገው እርምጃ በገንዘብ ሚኒስትሩ በክቡር አቶ አህመድ ሺዴ እና በሰላም ሚኒስትሯ በክብርት ወ/ሮ ሙፈሪያት ከሚል ታህሳስ 12 ቀን 2013 ዓ.ም ማብራሪያ ተሰጥቷቸዋል፡፡
ክቡር አቶ አህመድ ህግ የማስከበር እርምጃው የሰላማዊ ሰዎችን ህይወት ለአደጋ በማያጋልጥ ሁኔታ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተጠናቀቀ መሆኑን ገልጸው፣ የኢትዮጵያ መንግስት የሰብአዊ እርዳታ ጥረቱን በመደገፍ ረገድ የልማት አጋሮች ያበረከቱትን አስተዋጽኦ አድንቀዋል፡፡ ሁሉም የልማት አጋሮች ኢትዮጵያ የቀጠናው የሰላም ማእከል እንድትሆን ከጎኗ እንዲቆሙም ጥሪቸውን አቅርበዋል፡፡
አቶ አህመድ አያይዘውም በትግራይ ክልል ሀላፊነት በማይሰማው ወንጀለኛው ቡድን የወደሙትን የትራንስፖርት፣ የውሀ፣ የኤሌክትሪክና የቴሌኮሙኒኬሽን መሰረተ-ልማቶችን በመጠገን ክልሉን መልሶ በማቋቋም ወደ ነበረበት የመመለስ ጉዞ መጀመሩን አስረድተዋል፡፡
የመሰረተ ልማቶቹ መውደም ምግብና መድሀኒት የመሳሰሉትን የሰብአዊ ድጋፎችን ለማድረስ ጊዚያዊ ድልድዮችን በአስቸኳይ መገንባት የጠየቀ በመሆኑ በሰብአዊ ድጋፉ ምላሽ ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩንም አመልክተዋል፡፡
የትግራይ ክልል ጊዚያዊ አስተዳደርም የከተማ አስተዳደሮችን በማዋቀር ከቀበሌ ጀምሮ እስከላይ መዋቅር በመዘርጋት የተሻለ የሰብአዊ ድጋፍ ተደራሽነትና አፈጻጸም እንዲኖር ቁልፍ ሚና መጫወቱንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡
በማብራሪያው ላይ የተገኙት የሰላም ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል በበኩላቸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸው ከተባበሩት መንግስታት ጋር በቅንጅት የሰብአዊ እርዳታ ድጋፍ ለትግራይ ክልልና ጉዳት በደረሰባቸው አጎራባች የአማራና የዐፋር ክልሎች ሲያከናውን መቆየቱን አሰረድተዋል፡፡ በአንዳንድ ወረዳዎች የባንክ አገልግሎት በመጀመሩ፣ በአካባቢ ላሉ ገበያዎች አስፈላጊ ሸቀጦች ተደራሽ እንዲሆኑ ጥረት በመደረጉና የብሄራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ለ1.8 ሚሊዮን የክልሉ ህብረተሰብ የሰብአዊ እርዳታ ድጋፍ ማድረግ በመቻሉ በክልሉ ህይወት ወደቀድሞው ሁኔታ እየተመለሰ መሆኑን ሚኒስትራ አስረድተዋል፡፡
የልማት አጋሮች ድጋፍ ቡድን 30 አለም አቀፍ በይነ መንግስታትና የመንግስታት ትብበር የልማት አጋሮችን ያቀፈ ቡድን ሲሆን፣ አላመውም በኢትዮጵያ የፖሊሲ ውይይት እንዲጎለብት፣ የልማት አጋሮች ድጋፍ ውጤታማ እንዲሆን ማስተባበር እንዲሁም በብሄራዊ ፕላንና የዘላቂ ልማት ግቦች ላይ የክትትልና ግምምገማ ተግባሮችን ማከናወን ነው፡፡