ክቡር አቶ አህመድ ሺዴ- -የገንዘብ ሚኒስትር
አቶ አህመድ ሺዴ ከጥቅምት 2011 ዓ.ም. አንስቶ የኢፌዴሪ የገንዘብ ሚኒስትር ሆነው በማገልገል ላይ ናቸው፡፡ የገንዘብ ሚኒስትር ከመሆናቸው አስቀድሞ የትራንስፖርት ሚኒስትርና የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል፡፡ አቶ አህመድ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው ለረጅም አመታት አገልግለዋል፡፡
አቶ አህመድ ከስምንት ዓመታት በላይ የአገሪቱን ኢኮኖሚያዊ ትብብር እና የቀጠናዊ ልማት እና ውህደት አጀንዳዎችን በትጋት የመሩ የፋይናንስ ሚኒስትር ናቸው፡፡ ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው በሚያገለግሉበት ወቅት የመንግስትን የኢኮኖሚ ማሻሻያ ስራዎች በመደገፍ እና የላቀ አመራር በመስጠት ባለፉት አስርት ዓመታት ውስጥ አገሪቱ ላስመዘገበቻቸው የልማት እምርታዎች አስተዋፅዖ አበርክተዋል ፡፡ በአሁኑ ወቅት መንግስት በብዙ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት መስኮች የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ለማሻሻል እና ለማሳደግ ያለመውንና በትግበራ ላይ የሚገኘውን የሃገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ እየመሩ ነው፡፡
በተጨማሪም በክልል ደረጃ በተለያዩ ኃላፊነቶች የኢትዮጵያን መንግሥት በትጋት አገልግለዋል ፡፡ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ የፓርላማ አባል ናቸው ፡፡
አቶ አህመድ ከእንግሊዙ የሱሴክስ ዩኒቨርስቲ ከልማት ጥናት ኢንስቲትዩት በልማት ጥናት፣ አሳታፊነትና በማህበራዊ ለውጥ መስክ የማስተርስ ዲግሪ ከኔዘርላንድስ ሄግ ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ጥናት መስክ በገጠር ሃብት አስተዳደርና በሃብት ግጭት አፈታት በማስተርስ ዲግሪ፣ ከእንግሊዙ ግሪንዊች ዩኒቨርሲቲ በንግድ አስተዳደር የማስተርስ ዲግሪ ተቀብለዋል፡፡ አቶ አህመድ ከኢኮኖሚክስ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል፡፡
Copyright © 2021 MOF All Right Reserved