ሀገራችን ኢትዮጵያ ከ2013 እስከ 2022 የሚዘልቅ ‹‹ ፍኖተ ብልጽግና›› የተሰኘ የአስር አመት የልማት እቅድ ነድፋ የብልጽግና ጉዞ ጀምራለች፡፡
ከልማት እቅዱ አላማዎች ውስጥ በግንባር ቀደምትነት የተቀመጠው አላማ ‹‹የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ ገበያ-መር የኢኮኖሚ ሥርዓት በመከተል የግል ዘርፉን ጉልህ ሚናና ተሳትፎ በማሳደግ የበለጸገች ሀገር መገንባት›› የሚል ነው፡፡
ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ያስመዘገበችው ፈጣንና ተከታታይ እድገት በመንግስት ከፍተኛ ወጪ በተስፋፋ የመሰረተ- ልማት ዕድገት አማካኝነት የተመዘገበ ሲሆን ይህ በከፍተኛ ብድር እና እርዳታ የተሸፈነ የመንግስት ወጪ ተግባራዊ የሆነበት ሂደትና የተመዘገበው እድገት ለዓመታት የዋጋ ግሽበት ያስከተለና እድገቱም በተፈለገው መጠን ዘላቂና አስተማማኝ የስራ እድል ያልፈጠረ ነበር፡፡
ስለዚህም መንግስት የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ በማምጣት የኢኮኖሚ ስብራቱን ለመጠገንና መዋቅራዊ ሽግግሩን እውን ለማድረግ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያና የአስር አመት የልማት እቅድ አጽድቆ እየተጋ ይገኛል፡፡
እናም የእቅዱ ዋነኛ ዓላማና ትኩረቱ የግል-ክፍለ ኢኮኖሚውን ምርትና ምርታማነት እንዲሁም ተወዳዳሪነት በማሳደግ በሂደት የኢኮኖሚ እድገቱ በግሉ-ዘርፍ ወደሚመራበት ደረጃ ማሸጋገርና የተንሰራፋውን ስራ አጥነትንም ማቃል ይሆናል፡፡
ስለዚህም የ10 አመቱ መሪ የልማት እቅድ የሆነው ፍኖተ ብልጽግና እውን እንዲሆን መላው ህብረተሰብ፣ የግሉ ባለሀብት፣ የሲቪሉ ማህበረሰብ፣ የመንግሥትና የልማት አጋሮች የተቀናጀ ተሳትፎ ወሳኝ ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ህዝብ ብልጽግናን እመኛለሁ!