ለሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የተሰጠው የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት ፍቃድ ሂደት በእንግሊዙ የሽልማት ድርጅት አሸናፊ ሆኖ ተመረጠ፡፡

May 24, 2022

ግንቦት 16/2014 አዲስ አበባ - በገንዘብ ሚኒስቴርና በኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለስልጣን በተመራውና የቴሌኮም ዘርፍን ለውድድር ክፍት በማድረግ ለሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የተሰጠው አዲስ የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት ፍቃድ ሂደት በምርጥ የሕዝብ አገልግሎት ፕሮጀክት ምድብ እንግሊዝ በሚገኘው የልማት አጋር ሽልማት (Partnerships Awards) ድርጅት አሸናፊ ሆኖ ተመረጠ፡፡

 የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት ፍቃዱ አሰጣጡ ሂደት ልማት አጋር ሽልማት (Parnerships Awards) ድርጅት እ.ኤ.አ የ2022 አሸናፊ ሆኖ ተመረጠው በኢነርጂ፣ በውና በቴሌኮም ዘርፍ ምድብ ሲሆን ሽልማቱም  የተበረከተው ግንቦት 11/ 2014 ዓ.ም በእንግሊዝ ሀገር ለንደን ከተማ እ.ኤ.አ የ2021 እና 2022 ሽልማቶች አሸናፊዎች በተገለጹበት የሽልማት ሥነ-ሥርዓት ላይ ነው፡፡

የሽልማት ድርጅቱ ዳኞች የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት ፈቃድ የመስጠት ፕሮጀክት የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ በማበረታታት፣ በስራ እድል ፈጠራ እና በቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት መሻሻል ረገድ ለሀገር ልማት እና ለማህበረሰቡ የሚሰጠውን ትልቅ ፋዳ የተገነዘቡ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ፈቃድ የመስጠት ሂደቱም በጥንቃቄ እና ግልፅነትን በተላበሰ መልኩ የተመራ መሆኑ ፕሮጀክቱ እውቅናና ሽልማት እንዲያገኝ ያስቻሉት ቁልፍ መስፈርቶች መሆናቸው ታውቋል፡፡

የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት ፍቃድ ሂደቱ በአንደኛነት የተመረጠው ከአምስት የተለያዩ በአገልግሎት ዘርፍ በእጩነት ቀርበው ከነበሩ ፕሮጀክቶች መካከል ሲሆን በተለይ የአቡዳቢ የኃይል አቅርቦት የመንግስትና የግል አጋርነት ፕሮጀክትና እንግሊዝ ሀገር የሚገኘው የሳይዝዎል ሲ (Size well C) የኑክሌር ፕሮጀክትን አሸንፎ የኢትዮጵያው የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት ፍቃድ አሰጣጡ ሂደት መሸለሙ በዳኞቹ በኩል ለኢትዮጵያው ፕሮጀክት ያላቸውን ከፍተኛ ግምት የሚያሳይ መሆኑን ያመለክታል፡፡

282 Views