በመሰረታዊ የምግብ ሸቀጦች ላይ የጉምሩክ ቀረጥና ታክስ ማሻሻያ መደረጉ ተገለጸ

Sept. 3, 2021

ነሐሴ 28 2013 ዓ.ም ፡- በመሰረታዊ የምግብ ሸቀጦች ላይ የጉምሩክ ቀረጥና ታክስ ማሻሻያ መደረጉን የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ኢዮብ ተካልኝ ዛሬ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መብሰቢያ አዳራሽ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አብራርተዋል፡፡

መንግስት የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠርና የህብረተሰቡን የመግዛት አቅም ለማሳደግ የገንዘብና የፊስካል ፖሊሲ ማሻሻያዎችን እንዲሁም አስተዳደራዊ እርምጃዎችን ሲወስድ መቆየቱን ዶ/ር ኢዮብ አስረድተው በዚህም መሰረት የገንዘብ ሚኒስቴር ከፊስካል ፖሊሲ አኳያ የመሰረታዊ የምግብ ሸቀጦችን የጉምሩክ ቀረጥና ታክስ ማሻሻያ በማዘጋጀት ከነሐሴ 28 /2013 ዓ.ም ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜ በሚከተሉት መሰረታዊ የምግብ ሸቀጦች ላይ የጉምሩክ ቀረጥና ታክስ ማሻሻያ እንዲደረግ መወሰኑን አመልክተዋል፡፡

1. ስንዴ ከውጭ ሲገባ ከጉምሩክ ቀረጥና ታክስ ነጻ እንዲሆን፣

2. የምግብ ዘይት ከውጭ ሲገባም ሆነ በአገር ውስጥ ግብይት ሲፈጸምበት ከማንኛውም ቀረጥና ታክስ ነጻ እንዲሆን፣

3. ስኳር ከውጭ ሲገባም ሆነ በአገር ውስጥ ግብይት ሲፈጸምበት ከማንኛውም ቀረጥና ታክስ ነጻ እንዲሆን፣

4. ሩዝ ከውጭ ሲገባም ሆነ በአገር ውስጥ ግብይት ሲፈጸምበት ከማንኛውም ቀረጥና ታክስ ነጻ እንዲሆን፣

5. ፓስታ እና ማኮረኒ ከውጭ ሲገባም ሆነ በአገር ውስጥ ግብይት ሲፈጸምበት ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነፃ እንዲሆን፣ እንዲሁም

6. የደሮ እንቁላል ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነጻ እንዲሆን፣

ሚኒስትር ዴኤታው ማሻሻው ተግባራዊ ሲደረግ መንግስት በብዙ ቢሊዮን የሚገመት ገቢ እንደሚያጣ በተደረገው ጥናት ማረጋገጥ መቻሉን ጠቁመው የዋጋ ንረት በታክስ ብቻ የሚፈለገውን የዋጋ መቀነስ ስለማያመጣ አቅርቦትን ለመጨመር መንግስት በከፍተኛ ወጪ በመግዛት በዝቅተኛ ዋጋ ለህብረተሰቡ ከሚያቀርባቸው ከነዚህ መሰረታዊ የምግብ ሸቀጦች በተጨማሪ በሌሎች አካላት የሚገባውን በማከል አቅርቦቱ በከፍተኛ ደረጃ ይጨምር ዘንድ ለስድስት ወር ተፈቅዶ የነበረው ያለውጭ ምንዛሬ ሸቀጦችን የማስገባት አስራር ለሌላ ተጨማሪ ስድስት ወራት እንዲራዘም መደረጉንም ጨምረው ገልጸል፡፡

የንግስድ ፍሰቱ የተሳለጠ እንዲሆን የንግድ ሚኒስቴር ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመሆን አስፈላጊውን ክትትል ያደርጋል ብለዋል፡፡

ከእነዚህ በተጨማሪም መንግስት የዋጋ ግሽበቱን ለመቆጣተርና ገበያውን ለማረጋጋት ተጨማሪ የገንዘብ ፖሊሲን ጨምሮ ሌሎች የፖሊሲ ማሻሻያዎችን እንደሚወስድም ዶ/ር ኢዮብ ገልጸዋል፡፡

2362 Views