በመንግስት የበጀት የዝግጅት ሂደት የዜጎች ተሳትፎ እያደገ መምጣቱ ተገለፀ

Nov. 30, 2021

የገንዘብ ሚኒስቴር ከተለያዩ ተቋማት ለተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ትናንት ህዳር 16 2014 ዓ.ም በአዳማ ከተማ ባዘጋጀው የውይይት መድረክ በመንግስት በጀት ዝግጅትና ሂደት ዙሪያ የዜጎች ግንዛቤና ተሳትፎ እያደገ መምጣቱን በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የመንግስት ወጭ አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዳዊት ሽመልስ ገልጸዋል፡፡

ከህዝብ የሚሰበሰበውን የመንግስት ገንዘብ በአግባቡ በማስተዳደር ለታለመለት ዓላማ ለማዋል እንዲቻል ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ ላለፉት አስር ዓመታት ከፌዴራል እስከ ወረዳ ድረስ ባለው የአስተዳደር እርከን የፋይናንስ አሰራር ግልጽነትና ተጠያቂነት ሪፎርም በመተግበር ላይ እንደሚገኝም ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡

የሪፎርሙ ዋንኛ አላማ በመንግስት በጀት ሂደት ላይ የዜጎችን ግንዛቤ፣ ተሳትፎና የመረጃ ተደራሽነትን በማሳደግ ፍትሃዊ የሆነ ማህበረሰባዊ አገልግሎቶች ማዳረስና ለውጥ ማምጣት ሲሆን እስካሁን ድረስ በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ 2.8 ሚሊዮን ዜጎች በመንግስት በጀት ዝግጅት፣ ማጽደቅ፣ ትግበራና ግምገማ ላይ ግንዛቤና ተሳትፏቸው እያደገ መምጣቱን አቶ ዳዊት አብራርተዋል፡፡

ከፌዴራል ባለበጀት መስሪያ ቤቶች መካከል ለግማሽ ያህሎቹ የስልጠናና ክትትል ድጋፍ እየተደረገላቸው ሲሆን በመላ ሀገሪቱ 996 ወረዳዎች የበጀትና ወጭ መረጃዎችን ለዜጎች ይፋ ማድረግ እንደቻሉም ታውቋል፡፡

የፋይናንስ ግልጽነትና ተጠያቂነት ሪፎርም መተግበር ከጀመረበት ጊዜ እንስቶ የተገኙ መልካም አፈጻጸሞች ቢኖሩም የተለያዩ ተግዳሮቶችም ስለሚስተዋሉ ሪፎርሙ ውጤታማ እንዲሆን ባለድርሻ አካላት በትብብርና በቁርጠኝነት መስራት እንደሚገባቸውም ከውይይቱ ተሳታፊዎች ጋር መግባባት ላይ ተደርሷ፡፡

1114 Views