በንጽህና መጠበቂያዎች ላይ የቀረጥና ታክስ ማሻሻያ ተደረገ
March 9, 2021
ገቢ ምርቶች በሀገር ውስጥ እንዲመረቱ ለማስቻልና የሀገር ውስጥ ኢንዲስቱሪዎች እንዲበረታቱ በመሰረታዊ የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች ላይ በተለይም በወር አበባ ንዕህና መጠበቂያ ምርቶች ላይ የቀረጥና ታክስ ማሻሻያ መደረጉን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
በዚህም መሰረት የሴቶች ወር አበባ መጠበቂያ ( ሞዴስ) እንዲሁም የህፃናት ንዕህና መጠበቂያ ( ዳይፐር) በሀገር ወስጥ የሚያመርቱ ፋብሪካዎች ከውጭ የሚያስገቡት ጥሬ እቃ ከታክስ ነጻ እንዲሆን ተወስኗል፡፡
እነዚህ ከላይ የተጠቀሱትን የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች ከውጭ ሲገቡ ደግሞ ቀድሞ ከነበረውን ከፍተኛ የታክስ ምጣኔ ከ30 በመቶ ዝቅ ተደርጎ ታክሱ 10 በመቶ ብቻ እንዲሆን ተወስኗል፡፡
የቀረጥና ታክስ ማሻሻያው አላማ የንጽህና መጠበቂያ በቀላሉ ማግኘት በማስቻል ሴት ተማሪዎች ትምህርታቸውን ከወር አበባ ጋር በተዛመዱ ምክንያቶች እንዳያቋርጡና በትምህርት ቤት ወይም በሥራ ላይ የስነ-ልቦና ጭንቀት እንዳይደርስባቸው አስተዋዕኦ ለማድረግ ነው፡፡ በተጨማሪም የሀገር ውስጥ ምርትን ማጎልበት፣ የዋጋ ቅነሳ እንዲኖር ማስቻል፣ የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን ችግር ዘላቂ በመሆነ መንገድ መፍታትና ጥራት ያላቸው ምረቶች እንዲመረቱ በማድረግ ህብረተሰባችን ምርቱን ማግኘት እንዲችል ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት በሀገራችን የሴቶች የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ (ሞዴስ) አምራች ኢንዱስትሪዎች 8 ናቸው፡፡