በአውሮፓ ህብረት ፋይናንስ የሚደገፉ ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ ለሚያደርጉ ባለድርሻ አካላት ስልጠና ተሠጠ
March 18, 2022
መጋቢት 9/ 2014 ዓ.ም (አዳማ)፣ በገንዘብ ሚኒስቴር እና በአውሮፓ ህብረት ትብብር ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ለተውጣጡ የፕሮጀክት ማኔጀሮችና ባለሙያዎች ስልጠና ተሰጠ፡፡
የስልጠናው ዋና ዓላማ በአውሮፓ ህብረት ፋይናንስ የሚደገፉ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ከህብረቱ ጋር በተደረሰው የአሰራር ስምምነት መሰረት ፕሮጀክቶች የፋይናንስና የኮንትራት ሂደታቸው ቀልጣፋና ውጤታማ እንዲሆኑ ለማስቻል ያለመ ነው፡፡
ስልጠናው ከመጋቢት 5-9/ 2014 ዓ.ም ድረስ ለአምስት ተከታታይ ቀናት በአዳማ ከተማ የተሰጠ ሲሆን በዋናነት በአውሮፓ ህብረት ፕሮጀክቶች የግዥ ሂደት መሰረታዊ መርሆዎች፣ በፋይናንስ አስተዳደርና የወጭ ክፍያ እንዲሁም በተለያዩ ጊዚያት ከህብረቱ ከሚገኝ የፕሮጀክት ፋይናንስ ተጠቃሚ ለመሆን ጥራት ባላቸው የሂሳብ ሰነዶች አያያዝ፣ በፕሮፖዛል ዝግጅቶች እና በወቅታዊ ሪፖርት አቀራረብ ስርዓት ዙሪያ ያተኮረ ነበር፡፡
በየስልጠናው በአውሮፓ ህብረት የሚደገፉ ፕሮጀክቶችን በመተግበር ላይ የሚገኙ ከመንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ባለድርሻ አካላት የተውጣጡ 50 የሚደርሱ የፕሮጀክት ማኔጀሮችና ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
በስልጠናው ማጠናቀቂያ ሰለቀጣይ አሰራሮች የጋራ ግንዛቤ በመያዝ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ከህብረቱ የሚገኝን የፕሮጀክት ፋይናንስ በተሻለ ውጤታማነት ማስፈጸም እንደሚያስፈልግ መግባባት ላይ ተደርሶ ዛሬ መጋቢት 9/ 2014 ዓ.ም ለሰልጣኞች የተዘጋጀው የምስክር ወረቀት ከተሰጠ በኋላ ስልጠናው ተጠናቋል፡፡