በአዲሱ የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ቁጥር 1341/2016 በውሃ፣ በኤሌክትሪክ ኃይል እና በትራንስፖርት አቅርቦት ላይ ስለሚከፈል የተጨማሪ እሴት ታክስ
Aug. 29, 2024
- የውሃ እና የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት
የኤሌክትሪክ እና የውሃ አቅርቦት ላለፉት 22 ዓመታት ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነፃ ተደርጎ የነበረው አነስተኛ ገቢ ያለው የህብረተሰብ ክፍል ያለበትን የወጪ ጫና ለማርገብና ለማቃለል ታስቦ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ከአንድ ቤተሰብ ወርሃዊ አማካይ ፍጆታ በላይ ኤሌክትሪክ እና ውሃን በብዛት የሚጠቀመው የመክፈል አቅም ያለው የህብረተሰብ ክፍል በመሆኑ በተሰጠው መብት ይበልጥ ተጠቃሚ የሆነው ይህ የህብረተስብ ክፍል ነው፡፡ ይህ የህብረተሰብ ክፍል ታክሱ የሚያስከትልበት የወጪ ጫና ስለሌለ ድጋፉ ትርጉም አልነበረም፡፡
ድጋፉ ታሳቢ ያደረገውን የህብረተሰብ ክፍል ብቻ በሚጠቅም መልኩ ማስተካከያ ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነፃ የመሆኑ መብት ተፈጻሚ የሚሆነው የገንዘብ ሚኒስቴር በሚያወጣው መመሪያ መሰረት የሚወሰን ከአንድ ቤተሰብ ወርሃዊ ፍጆታ ያልበለጠ የኤሌክትሪክ እና የውሃ ፍጆታ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ ይህንን መጠን የሚወስን መመሪያ በጥቂት ቀናት ውስጥ ወጥቶ ተግባራዊ የሚደረግ ይሆናል፡፡
ስለዚህ መንግስት አነስተኛ ገቢ ያለው የህብረተሰብ ክፍል በመኖሪያ ቤቱ የሚጠቀመውን አማካይ ወርሃዊ የውሃና ኤሌክትሪክ ፍጆታ ከታክሱ ነፃ የሚያደርግ ሲሆን ከታክሱ ነፃ ከተደረገው በላይ የውሃና ኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚዎች ላይ የተጨማሪ እሴት ታክስ ተፈፃሚ እንዲሆን ያደርጋል፡፡
- የትራንስፖርት አገልግሎት
በተመሳሳይ መልኩ እንደ ውሃና ኤሌክትሪክ አገልግሎት የትራንስፖርት አገልግሎትም ላለፉት 22 ዓመታት ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነፃ እንዲሆን የተደረገው አነስተኛ ገቢ ያለው የህብረተሰብ ክፍል ለትራንስፖርት የሚያወጣው ወጪ እንዳይንር እንዲሁም በጭነት ተሽከርካሪዎች ላይ የሚከፈለው ታክስ የዕቃዎችን ዋጋ መናር እንዳያስከትል በማሰብ ነበር፡፡
ሆኖም ከህዝብ እና የጭነት ትራንስፖርት አገልግሎት ውጪ ለሌሎች የትራንስፖርት አገልግሎቶች የዚህ አይነቱን ድጋፍ ማድረግ ተገቢ ባለመሆኑ፣ መንግስት ማህበረሰቡ የብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎትን እንዲጠቀም የተለያዩ ድጋፎችን በመስጠት እያበረታታና መሰረተ ልማቶችንም እየገነባ በመሆኑ ለትራንስፖርት አገልግሎት የተሰጠው ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነፃ የመሆን መብት ባለሶስት እግር ተሽከርካሪን ሳይጨምር ከስምንት መቀመጫ በታች ያላቸውን ሌሎች ተሽከርካሪዎች እንዳይመለከት ተደርጓል፡፡
ስለዚህ መንግስት አሁንም የብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎት አቅርቦቶችን ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነፃ ያደረገ ሲሆን ባለሦስት እግር ተሽከርካሪን ሳይጨምር፣ አሽከርካሪውን ጨምሮ ከስምንት ሰው በታች የመጫን አቅም ያላቸውን ተሽከርካሪዎች በመጠቀም የሚሰጥ የትራንስፖርት አገልግሎት፣ የተጨማሪ እሴት ታክስ እንዲከፈልበት አድርጓል።