በአዲስ አመት አዲስ ተስፋ

Sept. 10, 2021

የኢትዮጵያ አዲስ አመት ተፈጥሮም ጭምር የሚለወጥበት ነው፡፡ በመስከረም ወር አዝመራው ያብባል፣ የደፈረሱ ወንዞች መጥራት ይጀምራሉ፣ አደይ አበባ ምድሪቱን ማልበስ ይጀምራል፣ የመስቀል ወፎች ከተደበቁበት ይወጣሉ፡፡ ለዚህም ነው የኢትዮጵያ አዲስ አመት የብሩህ ተስፋ መጀመሪያ ተደርጎ የሚታሰበው፡፡

የ2014 ዓ.ም አዲስ አመትም ከምንግዜውም በተለየ ሁኔታ የብሩህ ተስፋ ዘመን እንዲሆንልን የምንመኘው በ2013 ዓ.ም ያሳለፍናቸውን ፈተናዎች ተወጥተን ሰላም የሚሰፍንበትና ልማታችን ላይ የምናተኩርበት ዘመን እንዲሆንልን ካለን ጽኑ ፍላጎት ነው፡፡

መጪው አዲስ አመት በላያችን ላይ ያንዣበበው የህልውና አደጋ እንዲወገድ፣ ከቀያቸው በጦርነት ተፈናቅለው በየመጠለያው ያሉ ወገኖቻችን ወደየቤታቸው እንዲመለሱ፣ የወደሙ መሰረተ ልማቶች እንዲጠገኑ በአጠቃላይ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ህይወታችን እንዲታደስ ጠንክረን የምንሰራበት ዘመን ነው፡፡

የገንዘብ ሚኒስቴርና የተጠሪ ተቋማት አመራራና ሰራተኞችም በመጪው የ2014 አዲስ አመት ማክሮ ኢኮኖሚው እንዲረጋጋ፣ የመንግስት በጀት በአገባቡ ስራ ላይ አንዲውል፣ የመንግስት ሀብትና ንብረት ከብክነት በጸዳ መልኩ ለታሰበለት አላማ በቁጠባ ጥቅም ላይ እንዲውል እንዲሁም የውጭ ሀብት በተጠናከረ ሁኔታ እንዲሰባሰብ ተግተን የምንሰራበት ዘመን ነው፡፡

በመጨረሻም የገንዘብ ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራርና ማኔጅመንት መጪው አዲስ አመት ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ የሰላም፣ የጤናና የፍቅር እንዲሆን እየተመኘ የኢትዮጵያን ህልውና የማስቀጠሉ ተጋድሎ ተጠናክሮ እንዲቀጥልና ሀገራችን በልማትና እድገት ጎዳና እንድትራመድ ያላሰለሰ ጥረት እንደሚያደርግ ያረጋግጣል፡፡

መልካም አዲስ አመት   

9318 Views