በኢትዮጵያና በጃፓን መንግስታት መካከል የ25.4 ሚሊዮን ዶላር የፋይናንስ ድጋፍ ስምምነት ተፈረመ
March 10, 2023
መጋቢት 1 / 2015 ዓ.ም - በኢትዮጵያና በጃፓን መንግስታት መካከል ለመጠጥ ውሀ ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያና ለማዳበሪያ ግዢ የሚውል የ25.4 ሚሊዮን ዶላር የፋይናንስ ድጋፍ ስምምነት በገንዘብ ሚኒስቴር መሰብሰቢያ አዳራሽ ተፈረመ፡፡
ከፋይናንስ ድጋፉ ውስጥ 19.2 ሚሊዮን ዶላሩ በሀገሪቱ የተለያዩ ትንንሽ ከተሞች ለመጠጥ ውሀ ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ የሚውል ሲሆን 4.8 ሚሊዮን ዶላር ደግሞ 2500 ሜትሪክ ቶን የአፈር ማዳበሪያ ግዢ ለመፈጸም የሚውል መሆኑ ታውቋል፡፡
በመጠጥ ውሀ ፕሮጀክቱ በትንንሽና በገጠር ከተሞች የሚኖሩ ከ47ሺ በላይ ቤተሰቦች ተጠቃሚ የሚሆኑ ሲሆን የአፈር ማዳበሪያ ድጋፉም በአሁኑ ወቅት በአለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተውን የአፈር ማዳበሪያ የዋጋ ንረት በመጠኑ ለማረጋጋት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ታምኖበታል፡፡
የፋይናንስ ድጋፍ ስምምነቱን በኢትዮጵያ በኩል የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ ሰመሪታ ሰዋሰው የፈረሙ ሲሆን በጃፓን መንግሰት በኩል ደግሞ ሚስዝ ኢቶ ታካቶ በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ፈርመዋል፡፡