በኢትዮጵያ በቴሌኮም ኦፕሬተርነት ለመሳተፍ ፍላጎት ያላቸውን አለም አቀፍ ተጫራቾችን የሚያወያይ የቪዲዮ ኮንፈረንስ ተካሄደ

March 9, 2021

የካቲት 18 ቀን 2013 ዓ.ም አዲሰ አበባ፡ በኢትዮጵያ ሁለት የቴሌኮም ኦፕሬተሮችን ለመምረጥ የሚያስችልና በቴሌኮም ኦፕሬተርነት ለመሳተፍ ፍላጎት ያላቸውን አለም አቀፍ ተጫራቾችን የሚያወያይ የቪዲዮ ኮንፈረንስ ዛሬ በገንዘብ ሚኒስቴር እና በኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለሥልጣን አዘጋጅነት ተካሂዷል፡፡ የቪዲዮ ኮንፍረንሱ ለሁለት ቀናት የሚካሄድ ሲሆን ፍላጎት ያላቸው ተጫራቾች በሂደቱ ላይ ያላቸውን ጥያቄዎች ለመመለስና በሂደቱ ለመሳተፍ የሚያስፈልጓቸውን መረጃዎችን ለመስጠት ታቅዶ የተዘጋጀ ነው፡፡

የቪዲዮ ኮንፈረንሱን በንግግር የከፈቱት የገንዘብ ሚኒስቴር ክቡር አቶ አህመድ ሽዴ ዓለም አቀፍ የቴሌኮም ኦፕሬተሮች ወደ ገበያ እንዲገቡ የማድረጉ ጥረት ጤነኛ የገበያ ውድድር በመፍጠር የተሻለ የቴሌኮም አገልግሎት ማግኘት ከማስቻሉም በላይ ተደራሽነትን በማስፋት በመንግሥት የተቀመጠውን የዲጂታል ኢኮኖሚ ግብ የሚያሳካም እንደሚሆን አስረድተዋል፡፡

በቪዲዮ ኮንፈረንሱ ላይ ከገንዘብ ሚኒስቴር፣ ከጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት፣ ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ ከብሄራዊ ባንክ፣ ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንና ከኢትዮ ቴሌኮም የተውጣጡ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች የተሳተፉ ሲሆን ከኢትዮጵያ ኢኮኖሚና ከቴሌኮም አገልግሎት ጋር በተዛመደ ከመስሪያ ቤታቸው ተግባርና ሀላፊነት አንጻር ፍላጎት ላላቸው ተሳታፊዎች አስፈላጊውን መረጃ ሰጥተዋል፡፡

በዚህ የቪዲዮ ኮንፈረንስ ላይ በቴሌኮም ኦፕሬተርነትን በአለም አቀፍ ደረጃ አገልግሎት በመስጠት የሚታወቁ ድርጅቶች የተሳተፉ ሲሆን፣ ድርጅቶቹ ላነሷቸው ጥያቄዎችና አስተያየቶች ጉዳዩ በሚመለከታቸው የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ማብራሪያና ወቅታዊ መረጃ ተሰጥቷቸዋል፡፡

817 Views