በእንግሊዝ የፓርላማ አባል የተመራ የልዑካን ቡድን ኢትዮጵያ አረንጓዴ የኢኮኖሚ ልማት ለመገንባት እያደረገች ያለውን እንቅስቃሴ አደነቀ

March 9, 2021

ጥር 20 ቀን 2013 አዲስ አበባ፡ የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ በእንግሊዝ የፓርላማ አባል የተመራ የልዑካንን ቡድን ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡ በውይይቱ ወቅት አቶ አህመድ ሽዴ የኢትዮጵያ መንግስት የአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት የተለያዩ ስትራቴጂዎችን ቀርፆ ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በኢትዮጵያ የአስር ዓመት የልማት እቅድ ውስጥ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ከዋንኛ ምሰሶዎች መካከል አንዱ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡

በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ተነሳሽነት የተጀመረው የአረንጓዴ የደን ልማት ውጤት እያስገኝ እንደሆነም የገንዘብ ሚኒስትሩ ገልፀዋል፡፡

የወቅቱ የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ፕሬዝዳንት ክቡር አሎክ ሻርማ ለአየር ንብረት አጀንዳ ስኬታማነት የካርቦን ልቀትን መቀነስ ፣ የደን ጭፍጨፋን መከላከል ብሎም ለአየር ንብረት ለውጥ የሚያስፈልገውን ፋይናንስ ማሳደግ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡ በተጨማሪም በዚህ ረገድ ዓለም አቀፍ ትብብርን ማሳደግ አስፈላጊ መሆኑንም አፅንዖት ሰጥተዋል ፡፡

ክቡር አሎክ ሻርማ የደን መጨፍጨፍ በመቀነስ እና የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማትን ለማሳካት ኢትዮጵያ የምታደርገውን ጥረት አበረታተው ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ተምሳሌት መሆኗን ገልፀዋል ፡፡

በመጨረሻም አቶ አህመድ ሽዴ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭ የሆኑ አገራት የመቋቋም አቅም መገንባት እንዲችሉ ተጨማሪ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል ፡፡ እ.ኤ.አ ኖቬምበር 2021 በግላስጎው የሚካሄደው የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ጉባኤ ስኬታማ እንዲሆን ኢትዮጵያ የእንግሊዝን ጥረት ሙሉ በሙሉ እንደምትደግፍ ገልፀዋል ፡፡

582 Views