በዩኒቨርሲቲዎች የሚተገበሩ ፕሮጀክቶች ላይ የሚታየው የሀብት ብክነት እንዲስተካከል ማሳሰቢያ ተሰጠ

March 9, 2021

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 20፣ 2013 በሀገሪቱ በሚገኙ 10 የመጀመሪያ ትውልድ ዩኒቨርሲቲዎች በካፒታል ፕሮጀክቶች ላይ የሚታየው የሀብት ብክነት መስተካከል እንዳለበት የገንዘብ ሚኒሰቴር አሳሰበ፡፡

የገንዘብ ሚኒስቴር በከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ያሉ ፕሮጀክቶችን ዕቅድና አፈፃፀም የግምገማ ሪፖርት ላይ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር እና የዩኒቨርስቲዎች የበላይ አመራሮች በተገኙበት ውይይት አካሂዷል፡፡ በውይይቱ ትምህርት ሀገራዊ ራእያችን ለማሳካት የሚያስችለን የማስፈፀም አቅም በመገንባት ረገድ ቁልፍ በመሆኑ መንግስት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን መጠናከር ከፍተኛ ሀብት በመመደብ ዘርፉን ለማጎልበት የሚያስችሉ በርካታ ፕሮጅክቶች እንዲተገበሩ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል፡፡ ሆኖም ፕሮጀክቶቹ ወቅታቸውን ጠብቀው ባለመጠናቀቃቸው የሀብት ብክነት እየተከሰተ እንደሚገኝ ክቡር ዶ/ር ኢዮብ ተካልኝ የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ተናግረዋል፡፡ የሚኒስቴር መ/ቤቱ የፕሮጀክቶቹን አፈፃፀም በመከታተልና ያጋጠሟቸው ችግሮች ካሉ በመፍታትና ወቅታቸውን ጠብቀው እንዲጠናቀቁ በማስቻል በጀቱ ለታለመለት ዓላማ ማዋል እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል፡፡

በዚህ ዘርፍ በተለይም በቅርብ ዓመታት በርካታ ፕሮጀክቶች እንዲጀመሩ እና በበጀት እንዲካተቱ ተደርጓል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከ125 ቢሊዮን በላይ ብር ወጪ የሚጠይቁ ፕሮጀክቶች እንደሚገኙ በማስታወስ የእነዚህን ፕሮጀክቶች አፈጻጸም በማሻሻል የመንግስትን ሀብት ውጤታማነት ማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑ በውይይቱ ተገልጧል፡፡

በዚህ መሰረት በመተግበር ላይ ያሉ ነባር ፕሮጀክቶችን ተገቢውን ክትትልና ግምገማ በማካሄድ እስካአሁን የታዩትን ችግሮች በመቅረፍ ተጨማሪ ወጪና ጊዜ ሳይጠይቁ ማጠናቀቅ እና የታለመላቸውን ዓላማ እንዲያሳኩ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ዶ/ር ኢዮብ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል፡፡

በበጀት ላይ የሚገኙ ሆኖም ወደ ትግበራ ያልተሸጋገሩትን በተመለከተ ተገቢውን ጥናት በማካሄድ ከመተግበራቸው በፊት አስፈላጊነታቸውን መፈተሽና ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም አዲስ ፕሮጀክቶችን በተመለከተ በነባር ፕሮጀክቶች የታየው ችግር እንዳይደገም፣ የፌዴራል መንግስት ፕሮጀክቶች አስተዳደር እና አመራር ስርዓት አዋጅ እንዲጸድቅ የተደረገ መሆኑን በማስታወስ፣ ከዚህ በኃላ የሚተገበሩ አዲስ ፕሮጀክቶች በአዋጁ መሰረት ብቻ እንደሚተገበሩም ሚኒስትር ዴኤታው አስረድተዋል፡፡

የገንዘብ ሚኒሰቴር ዴኤታ ዶ/ር ኢዮብ ተካልኝ በውይይቱ ላይ እንደተናገሩት ቅድሚያ የሚሰጣቸው ፕሮጅክቶችን በመለየት በጀቱ ለታለመለት ዓላማ እንዲውል ዩኒቨርሲቲዎች ኃላፊነት መውሰድ እንደሚጠብቅባቸው ገለፀዋል፡፡ በቀጣይ በዩኒቨርሲቲዎች በሚሰሩቸው አዳዲስ ፕሮጅክቶች የመሰክ ጉብኝት ይደረጋልም ብለዋል፡፡

መሰል ውይይቶችም ከቀሪዎቹ ዩኒቨርስቲዎች ጋር በቀጣይነት ይደረጋል፡፡

528 Views