በደብረ ማርቆስ ከተማ አዲስ በሚገነባው የአውሮፕላን ማረፊያ እና የባህር ዳር ኤርፖርት ተርሚናል እድሳት ዙሪያ ላይ ውይይት ተካሄደ
March 22, 2021
የገንዘብ ሚኒስትር ክቡር አቶ አህመድ ሽዴ ከአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳደር ከክቡር አቶ አገኘሁ ተሻገር እና የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት በገንዘብ ሚኒስቴር ውይይት ተደረገ፡፡
ውይይቱ የደብረ ማርቆስ አየር ማረፊያ ግንባታን ለመጀመር በሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ በዚህ ረገድ ለሚገነባው ኤርፖርት ልማት የሚያስፈልገውን የወሰን ማስከበር ስራ የአማራ ክልል ከሶስተኛ ወገን አጥርቶ እንዲያስረክብ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡
በመሆኑም የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት የጀመረውን ጥናትና ዲዛይን በማጠናቀቅ በቀጣይነት ለሚካሄደው ግንባታ አስፈላጊው የጨረታ ሂደት እንዲካሄድ አቅጣጫ ተሰጥቷል፡፡
በተጨማሪም በህግ ማስከበር ዘመቻው ጉዳት የደረሰበትን የባህር ዳር የአውሮፕላን ማረፊያ ተርሚናል ወደ ቀድሞ አገልግሎቱ እንዲመለስ በአስቸኳይ እድሳት እንዲደረግለት ተወስኗል፡፡ ለዚህም የሚያስፈልገው ወጪን የፌዴራል መንግሰት እንደሚሸፍን በውይይቱ ላይ ተጠቅሷል፡፡