በገንዘብ ሚኒስቴር የ2015 በጀት አመት የስራ አፈጻጸምና የ3 አመት የልማትና ኢንቨስትመንት እቅድ ላይ ግምገማ ተካሄደ
Aug. 16, 2023
ነሐሴ 10/2015 ዓ.ም - የገንዘብ ሚኒስቴርና የተጠሪ ተቋማት የ2015 በጀት ዓመት የስራ አፈፃፀምና በቀጣዮቹ ሶስት አመታት ተግባራዊ በሚደረገው የልማትና የኢንቨስትመንት እቅድ ላይ የፕላንና ልማት ሚኒስትርና ባለድርሻ ተቋማት በተገኙበት በሚኒስቴሩ መሰብሰቢያ አዳራሽ ግምገማ ተካሂዷል፡፡
በግምገማው ወቅት የገንዘብ ሚኒስቴርና የተጠሪ ተቋማቱ የ2015 በጀት አመት አፈጻጸምና ከ2016 አስከ 2018 ዓ.ም የሚካሄደው የልማትና የኢንቨስትመንት እቅድ ቀርቦ የተገመገመ ሲሆን ከፕላንና ልማት ሚኒስቴርና ከጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት በመጡ አመራሮችና ባለሙያዎች ገንቢ አስተያየቶች ተሰጥተዋል፡፡
በቀረበው የስራ አፈጻጸም መሰረት የገንዘብ ሚኒሰቴር በበጀት ዓመቱ የመንግስት የልማት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎችን መነሻ ያደረገና በጥናት ላይ የተመሠረተ የፊስካል ፖሊሲ በማዘጋጀትና ተግባራዊነቱንም በመከታተል ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገትን በማረጋገጥ፣ የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት እንዲሁም የመንግስት የበጀት ጉድለት መጠን እና የእዳ ጫና እንዲቀንስ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት መከናወናቸው ተገልጽዋል፡፡
የመንግስት ገቢን ለማሳደግ የኢኮኖሚ ዕድገቱን መነሻ ያደረገ የሀገር ውስጥ የኤክሳይዝ ታክስ፣ የንብረት ታክስ፣ ኤክሳይዝ ቴምብር፣ እና የማህበራዊ ልማት ቀረጥ እና ኢንቨትመንት ማበረታቻ የታክስ ፖሊሲ ማሻሻያዎች ስራ ላይ መዋላቸውም ተመልክቷ፡፡
በበጀት ዓመቱ ከልማት አጋሮች ሊገኝ የሚችለውን የውጭ ሀብት ለማሰባሰብ በተለይም የዕርዳታ እና የብድር ግኝትና ፍሰት ለማሳደግ፣ የመልሶ ማቋቋምና ግንባታ ፕሮግራም ለመተግበር፣ የተለያዩ የኢኮኖሚ ትብብር እና አጋርነትን የማጠናከር ስራዎች መከናወናቸውም ተገልጽዋል፡፡
በተጨማሪም በዚሁ በጀት አመት የተመደበውን በጀት በጥሬ ገንዘብ ዕቅድ መሰረት ክፍያ የመፈጸም፣ ነቀፌታ ያለበትን የኦዲት ግኝት የመቀነስ፣ የተሻሻለ የመንግስት ፋይናንስ አስተዳደር ስርዓት የመዘረጋት እና የመንግስት ኤሌክትሮኒክ ክፍያን እና ግዢን የማስፋፋት ተግባራት መከናወናቸውም ተመላክቷል፡፡
በግምገማው ላይ የተገኙት የፕላንና ልማት ሚንስትሯ ዶ/ር ፍፁም አሰፋ እንደገለጹት የገንዘብ ሚኒስቴር የሚያወጣቸው ደንቦችና መመሪያዎች በሀገር ደረጃ ተጽእኖ ስላለቸው የሌሎች ተቋማትን ግብአት በማካተት ተግባራዊ ቢደረግ አጠቃላይ አፈፃፀምን ለመሻሻል እንደሚያግዝ አመልክተው የታክስ ማሻሻያዎች ውጤታማነትን ለማረጋገጥ አሰራርን በተከታታይ መፈተሸ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡
የገንዘብ ሚነስትሩ ክቡር አቶ አህመድ ሺዴ በበኩላቸው በበጀት ዓመቱ ከነበረው ጫና አንፃር የፊስካል አስተዳደሩ ጥሩ አፈጻጸም እንደነበረውና በእዳ አከፋፈል ፣ በግጭት የተጉዱ አካባቢዎችን መልሶ በማቋቋምና በፕሮጀክቶች አፈፃፀም የተከናወኑ አበይት ተግባራትን አንስተው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ከ2016 እስከ 2018 በጀት አመት በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄደው የሶስት አመት የልማትና ኢንቨስትመንት ዕቅድ የ10 አመቱ መሪ የልማት ዕቀድ ማስተግበሪያ ሲሆን የሀሪቱን ልማትና እድገት በማፋጠን ረገድ የላቀ አስተዋጽኦ እንዳለው ታምኖበታል፡፡