በግብርናው ዘርፍ የታዩ አበረታች ውጤቶችን ለማጠናከር በበጀት እንደሚደገፍ ተገለጸ
May 6, 2022
ሚያዚያ 28 / 2014 ዓ.ም - ለሶስተኛ ቀን ቀጥሉ በዋለው የፌዴራል ባለበጀት መስሪ ቤቶች የበጀት ስሚ መርሀግብር የግብርና ሚኒስቴርና በስሩ የሚገኙ ተጠሪ ተቋማት የ2015 በጀት ዓመት የበጀት ዕቅድ ያቀረቡ ሲሆን በግብርናው ዘርፍ የታዩ አበረታች ውጤቶችን ለማጠናከር ተገቢው የበጀት ድጋፍ እንደሚደረግም ተገልጻል፡፡
የበጀት ስሚ ፕሮግራሙን የመሩት የገንዘብ ሚኒስትሩ ክቡር አቶ አህመድ ሽዴ እንደገለጹት የግብርናውን ዘርፍ ለመጠናከር አቅም በፈቀደ መጠን የበጀት ድጋፍ አንደሚደረግ አመልክተው ግብርና ሚኒስቴር ለምግብ ዋስትና ስራ ለ2015 በጀት ዓመት የጠየቀው ገንዘብ ከተሰጠው ጣሪያ ከፍ ያለ በመሆኑ የበጀት ጥያቄው በተቀመጠው የበጀት ጣሪያ መሰረት እንዲስተካከል አቅጣጫ ሰጥተዋል፡፡
የገንዘብ ሚንስቴር ሚንስትር ዲኤታ ዶ/ር እዮብ ተካልኝ በበኩላቸው በግብርና ዘርፍ ከዚህ ቀደም የሚገባውን ያህል ትኩረት እንዳላገኘ ጠቁመው አሁን ግን ለዘርፉ መንግስት ተገቢውን ትኩረት በመስጠት ላይ መሆኑን ገልፀው፤ አሁን ላይ እየተገኙ ተጨባጭ ለውጦችን ይበልጥ ለማጠናከርና ለማስፋፋት መንግስት ያለውን ውስን ሀብት ጥቅም ላይ ያውላል ብለዋል፡፡
ዶ/ር ኢዮብ በተጨማሪም አጠቃላይ የሀብት ዕጥረት ስላለ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ተግባራት ለይተን መስራት አለብን ብለው በተለይ የተጀምሩ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቅቅ ትኩረት ሰጥተን መስራት አለብን ሲሉም ተናግረዋል፡፡