ባለፉት ሰባት የለውጥ አመታት ትልቅ የኢኮኖሚ ለውጥ መመዝገቡን የገንዘብ ሚኒስትር ገለጹ
April 2, 2025
መጋቢት 24 / 2017 ዓ.ም - ባለፉት ሰባት የለውጥ አመታት ትልቅ የኢኮኖሚ ለውጥ መመዝገቡን የገንዘብ ሚኒስትር ክቡር አቶ አህመድ ሺዴ ገለጹ፡፡
የገንዘብ ሚኒስቴርና የተጠሪ ተቋማት “ትናንት፣ ዛሬና ነገ ለኢትዮጵያ” በሚል መሪ ቃል የለውጡ መንግስት የተመሰረተበትን ሰባተኛ አመት ለመዘከር በተዘጋጀው መድረክ ክቡር አቶ አህመድ ሺዴ አንደገለጹት ባለፉት ሰባት የለውጥ አመታት ፕራይቬታዜሽንን በማጠናከር፣ የመንግስት የልማት ድረጅቶችን ውጤታማ በማድረግ፣ የዲጂታል ኢኮኖሚን በማጎልበት፣ የመሰረተ ልምት ግንባታዎችን በማስፋፋት፣ የእድገት ምንጮችን በማጎልበት፣ እድገትን ልማት ተኮር በማድግና የማክሮ ኢኮኖሚ ስብራቶችን በመጠገን በኢትዮጵያ ትልቅ የኢኮኖሚ ለውጥ መመዝገቡን አመልክተዋል፡፡
መጋቢት 24 የለውጡ መንግስት በይፋ የተመሰረተበትና የታላቁ እዳሴ ግድብ የመሰረት ድንጋይ የተጣለበት ታሪካዊ ቀን መሆኑን ክቡር ሚኒስትሩ ጠቅሰው የመጋቢት የለውጥ ፍሬዎችን የምንዘክረው ሁለንተናዊ ብልጽግናን እውን ለማድረግ ቁርጠኛ በመሆን ነው ብለዋል፡፡
በመድረኩ የኢኮኖሚ ሪፎርም ስራዎችን በተመለከተ የፓናል ውይይት የተካሄደ ሲሆን የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ፣ የፋይናንስ ዘርፍ ሪፎርም፣ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም በሚሉና ባለፉት ሰባት የለውጥ አመታት ስለተመዘገቡ ትሩፋቶች በገንዘብ ሚኒስቴርና ብሄራዊ ባንክ የኢኮኖሚ አማካሪዎች ማብራሪያ ቀርቦ ሰፊ ሙያዊ ውይትት ተደርጎባቸዋል፡፡
የገንዘብ ሚኒስቴር ተጠሪ ተቋም የሆነው የመንግስት ግዢ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ አስማረ ይገዙ በሰባቱ የለውጥ አመታት የተመዘገቡ ሁለንተናዊ ውጤቶችን አጠቃለው የመዝጊያ ንግግር በማድግ መድረኩ ተጠናቋል፡፡