ባለፉት ሶስት ወራት በመንግስት ገቢና ወጪ ረገድ ጤናማ የፊሲካል አስተዳደር ተግባራዊ መደረጉ ተገለጸ፡፡

Dec. 31, 2021

በ2014 በጀት አመት 2ኛ ሩብ ዓመት (ከጥቅምት-ታህሳስ) የ100 ቀን እቅድ አፈጻጸም በገንዘብ ሚኒስቴር በተገመገመበት ወቅት እንደተገለጸው በፌዴራል መንግስት ከሀገር ውስጥና ከልማት አጋሮች ለመሰብሰብ የታቀደውን የመንግስት ገቢ ለማሳካት ከፍተኛ ጥረት የተደረገ ሲሆን፣ አፈጻጸሙም መልካም እንደነበር ተመልክቷል፡፡

በዚህም መሰረት ፌደራል መንግስት ከጥቅምት እስከ ህዳር 2014 ባለው ሁለት ወራት ውስጥ ብቻ ከሀገር ውስጥ ገቢ ማለትም ታክስና ታክስ ካልሆኑ ገቢዎች 70.6 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ የቻለ ሲሆን ይህም የእቅዱ 89.3 በመቶ መሆኑ ታወቋል፡፡

ከጥቅምት እስከ ታህሳስ 2014 ዓ.ም ባለው ወቅት ከበይነ-መንግሥታዊ ተቋማት (Multilateral) እና ከመንግሥታት ትብብር (Bilateral) የልማት አጋሮች በእርዳታና በብድር በድምሩ 364 ሚሊዮን ዶላር የተገኘ ሲሆን 255.6 ሚሊዮን ዶላር ደግሞ ወደ ሀገር ውስጥ ፈሷል፡፡

በተመሳሳይ መልኩ ባለፉት ሶስት ወራት ከመንግሥት የልማት ድርጅቶች ትርፍ ድርሻ 3.8 ቢሊዮን ብር ለማስብሳብ ተችሏል፡፡

የመንግስት ወጪን በተመለከተም በዚሁ ወቅት ለፌዴራል መንግስት 73.3 ቢሊዮን ብር ወጪ የተደረገ ሲሆን ለብሔራዊ ክልላዊ መንግሥታት 33.6 ቢሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል፡፡ ስለዚህም በድምሩ 106.9 ቢሊዮን ብር ለፌደራልና ለክልል መንግስታት ክፍያ ተላልፏል፡፡ ስለዚህም ትኩረት ለሚሰጣቸው የመንግስት ወጪ ፍላጎቶች ቅድሚያ በመስጠት የተገኘውን ጥሬ ገንዘብ በአግባቡ ማስተዳደር መቻሉም ተመልክቷል፡፡

በመቶ ቀኑ እቅድ አፈጻጸም ግምገማ ላይ ከጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት፣ ከፕላንና ልማት ሚኒስቴር እንዲሁም ከገንዘብ ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት የተውጣጡ ሚኒስትሮች፣ ከፍተኛ አመራሮችና ባለሙያዎች የተገኙ ሲሆን በእቅድ አፈጻጸሙ ላይ የታዩ ጠንካራ ጎኖች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ደካማ ጎኖች ደግሞ የእርምት እርምጃ እንዲወሰድባቸው አስተያየትና አመራር ተሰጥቷል፡

1193 Views