"ብሔራዊ ጥቅም እና ጂኦስትራቴጂያዊ ቁመና" በሚል ርዕስ በገንዘብ ሚኒስቴር ውይይት ተካሄደ

Published: Oct. 16, 2025

ጥቅምት 6/ 2018 . - የገንዘብ ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት አመራሮችና ሠራተኞች በብሔራዊ ጥቅም እና በጂኦስትራቴጂያዊ ቁመና ርዕሰ ጉዳይ ላይ በተቋሙ መሰብሰቢያ አዳራሽ  ውይይት አደረጉ።

የውይይት መድረኩ አገራዊ ጥቅሞችን በዓለም አቀፍ መድረክ ለማስጠበቅ በሚያስችሉ ስትራቴጂያዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ሲሆን "ብሔራዊ ጥቅም እና ጂኦስትራቴጂያዊ ቁመና" በሚል ርዕስ የቀረበው ሰነድ አጠቃላይ የጂኦስትራቴጂክ ቁመናችንን እና ብሄራዊ ጥቅማችንን እንድንገዘብ የሚያስችልና እያጋጠሙን ያሉትን ተግዳሮቶች በመረዳት ሃገራዊ ጥቅሞቻችን ማረጋገጥ እንደሚገባ ከመግባባት ላይ የሚያደርስ ነው።

የውጭ ግንኙነት ኢንስቲትዩት ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት / ግዛቸው አስራት "ብሔራዊ ጥቅም እና የጂኦስትራቴጂያዊ ቁመና" በሚል ርዕስ ጥናታዊ ጽሑፍ አቅርበው ሰፊ ውይይት የተካሄደበት ሲሆን በጠናታዊ ጽሑፉም፣ አሁን ያለው ዓለም አቀፍ ሁኔታ አሮጌውን ሥርዓት አስወግዶ አዲስ ዓለም አቀፍ ሥርዓት ለመውለድ በሽግግር ላይ ያለበትና አገራት በባህር፣ በሳይበር እና በሌሎችም ጉዳዮች ከፍተኛ ፉክክር የሚያደርጉበት ፈታኝ ወቅት መሆኑን አስረድተዋል።

ሀገር ያለ ብሔራዊ ጥቅም ልትቀጥል እንደማትችል ጥናት አቅራቢው አጽንኦት ሰጥተው፣ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር ቀጣናዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን በጥልቀት መረዳት እንደሚገባ አብራርተዋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ዋንኛ ፈተናዎች ጂኦስትራቴጂያዊ ጉዳዮችና እና መልከዓምድራዊ እስረኝነት እንደሆኑ አመላክተው እነዚህን ተግዳሮቶች ለመሻገር  ዓለም አቀፋዊ ሕጎችን መሠረት በማድረግ ብሔራዊ ጥቅምን ማረጋገጥ ወሳኝ  መሆኑን ጠቁመዋል።

ለተግዳሮቶቹ ቁልፍ መፍትሄዎች ተብለው ከተጠቀሱት መካከልም "በታደሰ ቁመና አዲሱን ዓለም መዋጀት" የሚለው ዋነኛው ሲሆን፣ የመንግስት ተቋማት የብሔራዊ ጥቅምን ለማስከበር የተቋም ውጤታማነትን በማረጋገጥ፣ መልካም አስተዳደርን በማስፈን እንዲሁም ዲፕሎማሲያዊ ተጽዕኖ ፈጣሪነትን በማጎልበት የላቀ ሚና መጫወት እንደሚገባቸው ተገልጿል።

የውይይት መድረኩን የመሩት የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት / ሰመሬታ ሰዋሰው በሰጡት ማጠቃለያ፣  ያለንን የተፈጥሮ ሀብት፣ የህዝብ ቁጥር፣ ጅኦፖለቲካዊ አቀማመጥ እና የተደራጀ ተቋማዊ አቅም አስተሳስረን ተለዋዋጭ በሆነው ዓለማዊ ሁኔታ ውስጥ ብሔራዊ ጥቅማችንን ለማስጠበቅ ተግቶ መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል።

በመጨረሻም በቀረበው ገለጻ ላይ ከተሳታፊዎች ለቀረቡት ጥያቄዎችና አስተያየቶች ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷል።

 

47 Views