ኢትዮጵያና የአውሮፓ ህብረት በቀጣይነት በሚኖራቸው ትብብር ዙሪያ ምክክር አካሄዱ

March 18, 2021

በኢትዮጵያ መንግስትና በአውሮፓ ህብረት መካከል እ.ኤ.አ ከ2ዐ21- 2ዐ27 ድረስ ስለሚኖራቸው ትብብር በተመለከተ በተዘጋጀ ሰነድ ላይ ዛሬ በገንዘብ ሚኒስቴር ውይይት ተካሄደ፡፡ በውይይቱ የተሳተፉት የገንዘብ ሚኒስቴር፣የተለያዩ የፌዴራል መ/ቤቶች፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች  እና የአውሮፓ ህብረት ልዑክ ናቸው፡፡

ውይይቱም ያተኮረው የኢትዮጵያን የአስር ዓመት የልማት ዕቅድ እና የአውሮፓ ህብረት የልማት ፖሊሲን በረቂቅ ሰነዱ ውስጥ እንዲካተቱ በማድረግ ላይ ነው፡፡

የምክክር መድረኩን የመሩት የገንዘብ ሚኒስቴር ዴኤታ ክብርት ያስሚን ወሀብረቢ ኢትዮጵያና የአውሮፓ ህብረት የረጅም ጊዜ ጠንካራና ከጊዜ ወደጊዜ እያደገ የመጣ ትብብር ያላቸው መሆናቸውን በማስታወስ እስከአሁን ህብረቱ ለሚያደረገው ድጋፍ ያላቸውን ምስጋና አቅርበዋል፡፡ በተለይም በጤና፣በአየር ንብረት ለውጥ፣በምርጫ ድጋፍ፣በመንግስት ፋይናንስ አሰተዳደር እና በግብርና መሰክ የአውሮፓ ህብረት ባደረገው ድጋፍ በርካታ አመርቂ ውጤቶች እንደተገኙ ሚኒሰትር ዴኤታዋ አሰረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በድህረ ኮቶኑ ስምምነት መሰረት ከህብረቱ የተለያዩ የልማት ድጋፎች ከሚያገኙ የአፍሪካ፣ ካሪቢያንና ፓሰፊክ አገሮች በቀዳሚነት ከሚጠቀሱ ሀገራት መካከል አንዷ መሆኗ የመልካም ግንኙነት ማሳያ ነው ሲሉ በውይይቱ ወቅት ተናግረዋል፡፡

በውይይቱ ላይ የተነሱት ሀሳቦች በረቂቅ የትብብር ሰነዱ ላይ ተካተው እ.ኤ.አ. ከሜይ 2ዐ21 በፊት ለማጠናቀቅ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡

1001 Views