ኢትዮጵያ ሴት ስራ ፈጣሪዎችን ለማገዝ የሚያስችል የብድር ስምምነት ከዓለም ባንክ ጋር ተፈራረመች
March 8, 2021
የኢትዮጵያ መንግስትና ዓለም ባንክ በጥቃቅንና አነስተኛ ስራ ዘርፍ የተሰማሩ የሴት ስራ ፈጣሪዎችን ገቢ ለማሳደግ እና የስራ ዕድል ለማስፋት የሚያስችል የ100 ሚሊየን ዶላር / የ3.8 ቢሊዮን ብር/ የብድር ስምምነት ታህሣሥ 16/ 2013 ዓ.ም በገንዘብ ሚኒስቴር የስብሰባ አዳራሽ ተፈራረሙ፡፡
ኮቪድ 19 ስራቸው ላይ ጉዳት የደረሰባቸው የንግድ ተቋማት አስፈላጊውን የገንዘብ ድጋፍ በወቅቱ እንዲያገኙ በማስቻል የንግድ ተቋማቱን ህልውና በመታደግ የዜጎችን ህይወት ማስቀጠል እንደሚያስቸል የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ት ያስሚን ወሀብሬቢ የፕሮጀክት ስምምነቱ በተፈረመበት ወቅት አስረድተዋል፡፡ ፕሮጀክቱ ተጠቃሚዎች ያሉበትን ሁኔታ ከግንዛቤ በማስገባት የፋይናንስ ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችሉ አሰራሮችን በማስተዋወቅ ጥቃቅንና አነስተኛ ድርጅቶች የሚያጋጥማቸውን ተግዳሮቶች መሻገር ያስችላል ብለዋል፡፡
ሚስተር ኦስማን ዲዮን የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር በበኩላቸው ባንኩ የገንዘብ እጥረት ያለባቸውን ጥቃቅንና አነስተኛ ድርጅቶች ብድር የሚያገኙበትን መንገድ በማመቻቸት ያጋጠማቸውን ችግሮች ለመቅረፍ ሲደረግ የቆየውን ድጋፍ ዘላቂ አንዲሆን የሚያግዝ፣ የድርጅቶቹን ህልውና ለማስቀጠል የሚረዳና የስራ እድል ለመፍጠር የሚያስችል መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ፕሮጀክቱ ጥቃቅንና አነስተኛ ድርጅቶችን ለሚመሩ ሴቶች የንግድ ስራ ክህሎት ስልጠና እንዲያገኙ የሚያደርግ ሲሆን፣ በተጨማሪም ለቴክኒክና ሙያ ተቋማትና ለጥቃቅንና አነስተኛ ንግድ ቢሮዎች የቴክኒክ ድጋፍም ለማድረግ ያለመ ነው፡፡
የፋይናንስ ድጋፉ ከዚህ ቀደም በፕሮጀክቱ አማካኝነት የተገኙ ውጤቶችን ለማስቀጠልና በተለይም ፕሮጀክቱ በሴቶች የተቋቋሙና የሚመሩ ድርጅቶችን ለመድረስ የተከተለው አካሄድ ዘላቂ እንዲሆን ያስችላል፡፡ ሚስተር ኦስማን ዲዮን ፕሮጀክቱ እ.አ.አ. እስከ ኖቬምበር 2020 ከ16 ሺህ በላይ ለሆኑ የንግድ ድርጅቶች ብድር የሰጠ መሆኑን ጠቅሰው ፕሮጀክቱ ከነበረው ተሞክሮ በመነሳት የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት የማበደር አቅማቸውን በማጠናከር የብድር አገልግሎት በቀላሉ ለማግኘት እድል የሌላቸውን የማህበረሰብ ክፍሎች ዘንድ ለመድረስ እንደሚቻል አሳይቷል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ የመረጃ አሰባሰብ ዘዴዎችን በመከተል ለመጀመሪያ ጊዜ የብድር አገልግሎት የሚያገኙ ተጠቃሚዎች ያለ ከፍተኛ ማስያዣ (ኮላተራል) ብድር ማግኘት የሚችሉባቸውን መንገዶች ፕሮጀክቱ ማመቻቸቱን አስረድተዋል፡፡
ስምምነቱ በገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ት ያስሚን ወሀብሬቢ እና በሚስተር ኦስማን ዲዮን የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ፣ የሱዳን፣ የደቡብ ሱዳንና የኤርትራ ዳይሬክተር የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክና የዓለም ባንክን በመወከል ተፈርሟል፡፡