ኢትዮ ቴሌኮም የደንበኞቹ ቁጥር ከ60 ሚሊየን ማለፋን አስታወቀ
March 3, 2022
የኢትዮ- ቴሌኮም የግማሽ ዓመት አፈፃፀም ዛሬ የካቲት 21 2014 ዓ.ም በሂልተን ሆቴል በገንዘብ ሚኒስቴርና በመንግስት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር በተገመገመበት ወቅት የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ የድርጅታቸው አጠቃላይ የደንበኞች ቁጥር 60 ነጥብ 8 ሚሊየን መድረሱን አስታውቀዋል፡፡
ዋና ስራ አስፈፃሚዋ አንዳሉት በዘንድሮ ግማሽ ዓመት ድርጅቱ 28 ቢሊየን ብር ግቢ ማገኘቱን ተናገረው፤ 74 ነጥብ 8 ሚሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ገቢ ማግኘቱንና ከስምንት ወር በፊት ስራ ላይ ባዋለው የቴሌ ብር አገልግሎት 13 ነጥብ 1 ሚሊየን ደንበኞችን በማፍራት 16 ነጥብ 6 ሚሊየን ክፍያዎች በመተግበሪያው አማካኝነት መደረጉንና በገንዘብ ረገድም የ5 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ልውውጦች መደረጋቸውን ተናግረዋል፡፡
ወጪውን ለመቀነስ እንዲያስችለው ‹‹ዱቱሴቭ›› አሰራርን ተግባራዊ በማድረግ 1 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ወጪ ማስቀረት ችያለሁ ያለው ድርጅቱ፣ 2 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ለዕዳ ክፍያ ማዋሉን፣ እንዲሁም 12 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር የታክስ ክፍያ መፈፀሙንም ገልጿል፡፡
ከግማሽ ዓመቱ ዕቅዴ 86 በመቶውን ነው ያሳካሁት ያለው ድርጅቱ የፀጥታ ችግር፣ የመስረተ ልማትና ንብረት ጉዳት፣ በክልሎች አግባብ ያልሆነ ካሳ ጥየቃና የባንክ ሂሳብ መዘጋት ለስራዬ ዋና ዕንቅፋት ነበሩ ሲልም አስታውቋል፡፡
የግምገማ መድረኩን የመሩት የገንዘብ ሚኒስቴር ሚንስትር ክቡር አቶ አህመድ ሽዴ እንዳሉት ኢትዮ ቴሌኮም ባለፋት 6 ወራት ውስጥ አገልግሎቱን በማስፋፋት፣ የአግልግሎቱን ጥራት በማሻሻል፣ የገጠሙትን ፈተናዎች ለማለፍና በተለይ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት በኩል ጠንክራ ስራ ሰርቷል ብለዋል፡፡
ክቡር አቶ አህመድ በተጨማሪም ኩባንያው ይበልጥ ትርፋማ እንዳይሆን ምክንያት የነበሩ ደንቦችና አሰራሮችን መንግስት ለማሻሻል መስራቱን ተናግረው፤ ወደፊትም ለሚገጥሙት ችግሮች በጋራ መፍትሔ ለመስጠት ይሰራል ብለዋል፡፡
በወጪ ቅነሳ በኩል ኩባንያው ጥሩ መሻሻል አሳይቷል ይህ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ያሉት አቶ አህመድ ሽዴ በቀጣይ ኩባንያው ራሱን ለውድድር በበቂ ሁኔታ ማዘጋጀት እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡