የመሰረታዊ አገልግሎቶች አሰጣጥና ማህበራዊ ተጠያቂነት ፕሮግራሞች የጋራ ግምገማ ተጀመረ

Nov. 22, 2022

ህዳር 13 / 2015 ዓ.ም - በገንዘብ ሚኒስቴርና በልማት አጋሮች ትብብር የሚካሄደው የመሰረታዊ አገልግሎቶች አሰጣጥና ማህበራዊ ተጠያቂነት ፕሮግራሞች አፈጻጸም የጋራ ግምገማ በገንዘብ ሚኒስቴር የመሰብሰቢያ አዳራሻ ተጀመረ፡፡

የጋራ ግምገማው አላማ በመሰረታዊ ማህበራዊ አገልግሎቶች ማለትም በትምህረት፣ በጤና፣ በንጹህ መጠጥ ውሃ፣ በግብርናና በገጠር መንገድ ዘርፎች የክልል መንግስታትና የፌዴራል መስሪያ ቤቶች በሚያቀርቡት ሪፖርት መሰረት በመላ ሀገሪቱ የተከናኑ ተግባራን ከእቅዱ አንጻር መገምገም ነው ፡፡

ከመሰረታዊ ማህበራዊ አገልግሎቶች በተጨማሪም የጋራ ተጠቃሚነትን በፍትሀዊ ማህበራዊ አገልግሎት ማጎልበት በሚል ማእቀፍ መሰረት ተግባራዊ የሚደረገውን  የማህበራዊ ተጠያቂነት ፕሮግራም አፈጻጸም የሚገመገም ሲሆን ለሁለት ቀናት በሚካሄደው የጋራ ግምገማ ደሀ ተኮር የተባሉት የአምስቱ መሰረታዊ  ማህበራዊ አገልግሎት ዘርፎች፣ በዘላቂነት ዘርፎቹን ፋይናንስ ስለማድረግና የዜጎች ተሳትፎ ጉዳዮች ከፍተኛ ትኩረት ይሰጣቸዋል፡፡

በገንዘብ ሚኒስቴር የቻናል አንድ ፕሮግራሞች ማስተባባሪያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ደጉ ላቀው የጋራ ግምገማ መድረኩን ሲመሩ እንደገለጹትም የጋራ ግምገማውን በየጊዜው ማካሄድ ያስፈለገው ዜጎች ጥራት ያለው መሰረታዊ ማህበራዊ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ ለማስቻልና በማህበራዊ ተጠያቂነት ፕሮግራም በኩል ደግሞ የዜጎችን ተሳትፎና ባለቤትነት ለማረጋገጥ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

በጋራ የግምገማው መድረክ የመሰረታዊ አገልግሎቶች አሰጣጥና ማህበራዊ ተጠያቂነት ፕሮግራሞች አፈጻጸም ምንም እንኳ ባለፉት ጊዚያት በግጭትና በኮቪድ ምክንያት ተጽዕኖ ቢደርስበት አጠቃላይ አገራዊ አፈጻጸሙ ተስፋ ሰጪ እንደሆነ ተመልክቷል፡፡

በዚህ የመሰረታዊ  አገልግሎቶች አሰጣጥና ማህበራዊ ተጠያቂነት ፕሮግራሞች ጋራ ግምገማ መድረክ ከሁሉም ብሄራዊ ክልላዊ መንግሰታትና ከተመረጡ የፌዴራል መስሪያ ቤቶች የተውጣጡ የዘርፉ ባለሞያዎች ሪፖርታቸውን የሚያቀርቡ ሲሆን የመንግስት ገቢና ወጪ አፈጻጸም፣ የመንግስት ፋይናንስ አስተዳዳር፣ የመንግስት ግዢና ንብረት አስተዳዳር፣ የመንግስት ፋይናንስ ግልጽነትና ተጠያቂነት ርዕሰ ጉዳዮች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸው ታውቋል፡፡

1260 Views