የመንግስት ልማት ድርጅቶች አለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት አቀራረብን ተከትለው እንዲሰሩ ማሳሰቢያ ተሰጠ

March 9, 2021

የገንዘብ ሚኒስቴር የመንግስት የልማት ድርጅቶች በአለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት አቀራረብ ደረጃዎች (International Financial Reporting Standards- IFRS) አተገባበር ተከትለው እንዲሰሩ አሳሰበ፡፡

የውይይቱ ዋነኛ ዓላማ የመንግስት የልማት ተቋማት የአለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት አቀራረብ ደረጃዎች (IFRS) አተገባበር ሁኔታ እና ያሉበትን ደረጃ ለማወቅ የተካሄደ ነው፡፡ ተቋማቱ የIFRS ትግበራ በተመለከተ የሚገኙበትን ደረጃ በሪፖርት መልክ አቅርበዋል፡፡

የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ኢዮብ ተካልኝ ለውይይቱ ተካፋዮች የመክፈቻ ንግግር ባደረጉበት ወቅት እንደተናገሩት አለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት አቀራረብ ደረጃዎች አተገባበር በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ እየተተገበረ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡

በተቋማት ከትግበራው ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ ያለውን አጠቃላይ የአተገባበር ሂደት በማየት በቀጣይ በሙሉ አቅም መስራት እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል፡፡ ይህንን የሂሳብ አያያዝ በመጠቀም በዓለም ካፒታል ገበያዎቸን ላይ ለመድረስ እና አዳዲስ የንግድ እድሎት እንዲፈጠሩ ትልቅ ሚና እንዳለው ሚኒስትር ዴኤታው አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሂክመት አብደላም በበኩላቸው የፋይናንስ ሪፖርት ተግባራዊ ተደረገበት ጊዜ አንስቶ ለተቋማት የበላይ ሀላፊዎች እና ባለሞያዎች ስልጠና በመስጠት፣ በዘርፉ አማካሪዎችን በመቅጠር፣ ትግበራውን ቀድመው ከጀመሩ ሌሎች ተቋማት ልምድ እንዲካፈሉ የማድረግ ስራ መከናወኑ ተናግረዋል፡፡ በዚህም የተነሳ አብዛኛው የመንግስት ልማት ድርጅቶች አሰራሩን እየተገበሩ እንደሆነ እና ይህም አሰራራቸውን ቀልጣፋና ውጤታማ እንዲሆን አስችሏል ብለዋል፡፡

በውይይቱ የተሳተፉ ተቋማት ሪፖርታቸውን ባቀረቡበት ወቅት እንደገለጹት አዋጅ ቁጥር 847/2006 የህዝብን ጥቅም ከማስጠበቅ አኳያ ዋነኛ ዓላመው አድርጎ የተነሳ መሆኑን ጠቅሰው በተቋሞቻቸውም የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውኑ የቆዩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የልማት ድርጅቶቹ አለም አቀፍ የሂሳብ አያያዝ ቦርድ IASB (International Accounting Standard Board) ያወጣቸውን ደረጃዎች እና የአተገባበር ሁኔታውን ከመረዳት አኳያ በአንዳንድ ተቋማት የግንዛቤ ችግር መኖሩ፣የተዘጋ የፋይናንስ ሂሳብ አለመኖር እና ከሰርቨር አለመኖር ጋር ተያይዞ የተለያዩ ተግዳሮቶች እንደገጠማቸው ገልፀዋል፡፡

ዶ/ር ኢዮብ ተካልኝ ከተወያዮቹ ለተነሱት ሃሳቦች አስተያየት በሰጡበት ወቅት ሁሉም ተቋም የIFRS ትግበራ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ መጨረስ ይኖርባቸዋል በሚል አሳስበዋል፡፡ በሀገር አቀፍ ደረጃ የአንዱ ተቋም ድክመት የሌላውን ጥንካሬ ስለሚሸረሽረው መልካም ተሞክሮ ያሳዩ ተቋማት ለሌሎች ልምዶቻቸውን በማካፈል መስራት ይኖርባቸዋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ተቋም ተኮር ጥያቄዎች በተመለከተም በየደረጃው ምላሽ እንደሚሰጥበት ገልጸዋል፡፡

1185 Views