የመንግስት እና የግሉ ዘርፍ አጋርነት ዙሪያ ለባለድርሻ አካላት ስልጠና ተሰጠ

April 6, 2021

 

በመንግስትና በግሉ ዘርፍ አጋርነት ( Public Private Partnership) ዘርፍ የሚንቀሳቀሱ ባለድርሻ አካላትን አሰራር ለማሻሻልና ለማጎልበት ያለመ ስልጠና በቢሾፍቱ ከተማ ተካሂዷል።

በስልጠናው የተገኙት ላይ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ያስሚን ወሀብረቢ እንደገለፁት የመንግስትና የግል አጋርነትን በአግባቡ የተገነዘበ መዋቅራዊ አደረጃጀት ለመፍጠርና ተግባራዊነቱን ለማረጋገጥ ጉዳዩን ለሁሉም የዘርፉ ተዋናዮች ለማሳወቅ የስልጠና መድረኩ እንደተዘጋጀ አመልክተዋል።የመንግስትና የግል አጋርነት በመንግሥት ፖሊሲ ትኩረት ውስጥ ተካቶ፥ በአዋጅ ተደግፎና የአሰራር ማንዋል ተዘጋጅቶለት የትግበራ እንቅስቃሴ እንደተጀመረ ጠቁመው በተለይ በፀሐይ ሀይል ዙሪያ የፕሮጀክቱ ጥናት ተደርጎ ለትግበራ ዝግጁ መደረጉን አስረድተዋል።

የግልና የመንግስት አጋርነት የሀገር ውስጥ ብድርን በመጠቀም በራስ አቅም የሚከናወን የውሀ፥ የኤሌክትሪክ፥የመንገድና መሰል የመሰረተ ልማት ለማስፋፋት የሚከናወን በመሆኑ ቅንጅታዊ አሰራር መፍጠር ወሳኝ እነደሆነ ገልፀዋል። የፕሮጀክት አላማዎቻችን የሚሳኩ እንዲሆኑ ማድረጉ የሀገሪቱንና የህብረተሰቡን ወደፊት የሚወስኑ ስለሆነ የላቀ ትኩረት እንደሚሹ ጨምረው ገልፀዋል።

የመሠረተ ልማት ሥርዓቱን ጨምሮ የአገሪቱን የልማት ግቦች ከማሳካት አንጻር የግሉ ሴክተር ወሳኝ ስትራቴጂያዊ አጋር በመሆኑ፤ የዘርፉን እምቅ አቅም ለመጠቀም በአዋጅ ቁጥር 1076/2010 ቁጥር ግልጽነትን፣ ፍትሐዊነትን እና ዘላቂነትን በማስፈን እና በግሉ ዘርፍ የፋይናንስ አቅም የሚገነቡ የመሠረተ-ልማት ፕሮጀክቶችን ለማበረታታት የሚረዳ አመቺ የሕግ ማዕቀፍ በማስፈለጉእንደተዘጋጀ በመንግስት የግል አጋርነት አዋጅ ላይ ተጠቅሷል።

በመድረኩ የመንግስትና የግል አጋርነት ዳይረክተር ጀነራል አቶ ጥላሁን ሀይሌ የመንግስትና የግል አጋርነትን ተግባራዊ ለማድረግ በሰው ሀይል፥በአሰራርና በአደረጃጀት ላይ አተኩሮ መስራት አስፈላጊ መሆኑን ለተሳታፊዎች ገለፃ አድርገዋል።መሰረተ ልማትን በግሉ ዘርፍ ቀጥተኛ ተሳትፎ ለመከወን መግአ የሚጫወተው ሚና አይነተኛ እንደሆነ ከመድረኩ የተነሳ ሲሆን ለጋራ ፍላጎት፥ለጋራ ሀላፊነትና ሀብትን በጋራ በመጠቀምና ሀላፊነትን በጋራ በመወጣት የመሰረተ ልማት ተደራሽነት ማረጋገጥ እንደሚቻል ተመልክቷል።

ስልጠናው ለሚመለከታቸው የባለድርሻ አካላት በተከታታይ እንደሚሰጥ ከመድረኩ አስተባባሪዎች ተጠቁሟል።

1145 Views