የመንግስት የፋይናንስ አስተዳደር ስርዓት ሪፎርም ለማድረግ የገንዘብ ሚኒስቴር አዲስ ስትራቴጂክ ዕቅድ ይፋ አደረገ
March 9, 2021
የገንዘብ ሚኒስቴር የመንግስት ፋይናንስ አስተዳደር ለማሻሻል የመንግስትን የበጀት ፣ የፋይናንስ እና የሂሳብ አያያዝ ስራዎችን የሚደግፍ የተቀናጀ የፋይናንስ አስተዳደር መረጃ ስርዓት (IFMIS) ፕሮግራም ተደራሽነትን ለማሳደግ እንደሚሰራ አስታወቀ፡፡
ይህ የተገለጸው አዲሱ የIFMIS ስትራቴጂክ እቅድ (እ.ኤ.አ.2021-2025) ለዋና ዋና ባለድርሻ አካላት በቀረበበት ወቅት ነው፡፡ በሁለተኛው የስትራቴጂክ ዘመን ሊደረስባቸው የታለሙ ቁልፍ ውጤቶችን ያብራሩት የገንዘብ ሚኒስትር የIFMIS ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ አቶ ነጋ መንግስቱ እንደተናገሩት የፕሮግራሙን ውጤታማነት ለማሳደግ፣ የተሻሻሉ መሠረተ ልማቶች በመጠቀምና ተቋማዊ አሠራሮችን የበለጠ በማሳደግ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ተጨማሪ 760 ጣቢያዎችን ለመድረስ የሚኒስቴር መ/ቤቱ እየሰራ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
የIFMIS ስትራቴጂክ ዕቅድ በሚኒስቴር መ/ቤቱ እየተከናወኑ ከሚገኙ የተለያዩ የፋይናንስ አስተዳደር ማሻሻያዎች ጋር የተያያዘ እና ለኢትዮጵያ ማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋት፣ የህዝብ አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል፣ ለበጀት አመዳደብ፣ የገቢ አሰባሰብ እና የወጪ አያያዝን ለማዘመን የበኩሉን አስተዋፅኦ በማበርከት ተጠያቂነት የሰፈነበት የመንግስተ ፋይናንስ ስርዓትን ለመፍጠር ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው ተብራርቷል፡፡
አቶ ነጋ በመጀመሪያው የስትራቴጂክ ዘመን (እ.ኤ.አ 2016-2020) የIFMIS ፕሮግራም ወደ 156 ጣቢያዎች እንደተዘረጋ፣ ስለፕሮግራሙ ለ14,773 የመጨረሻ ተጠቃሚዎች ስልጠና መሰጠቱን፣ የፕሮግራሙን ትግበራ ለመደገፍ የሚያስችል በቂ የውስጥ አቅም መገንባቱን አብራርተዋል፡፡
በተጨማሪም በአሁኑ ወቅት ከፌዴራል መንግሥት በጀት ውስጥ 84% የሚሆነው በIFMIS እየተዳደረ ነው ብለዋል፡፡ IFMIS በመጀመሪያው ስትራቴጂካዊ ወቅትም ከ25 ሚሊዮን በላይ ግብይቶችን አስተናግዷል፡፡ ስትራቴጂካዊ ዕቅዱ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ IFMISን ከሌሎች የኤሌክትሮኒክስ ግዥ እና ገቢ ጋር ከመሳሰሉ የመረጃ ስርዓቶች፣ ከብድር አስተዳደር፣ የፋይናንስ መረጃ ትንተና ፣ ከብሄራዊ ባንክ፣ከንግድ ባንክ እንዲሁም ከገቢዎች ጋር የማዋሃዱን ስራ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
የIFMIS ስኬታማ ትግበራ ወቅታዊ ፣ ተገቢ እና አስተማማኝ የፋይናስ መረጃዎችን በቀላሉ ለማግነት ያስችላል፡፡