የመንግስት ግዢና ንብረት አስተዳደር ስርዓትን ለማሻሻል የሚያግዝ የምክክር መድረክ ተካሄደ

March 9, 2021

የመንግስት ግዢንና ንብረት አስተዳደር ውጤታማና በዕቅድ የሚመራ ለማድረግ የፌዴራል ባለበጀት መስሪያ ቤቶች በዛሬው ዕለት በገንዘብ ሚኒስቴር እየመከሩ ነው፡፡
በመድረኩ የተገኙት የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ኢዮብ ተካልኝ እንደተናገሩት የፌዴራል መንግሥት ባለበጀት መ/ቤቶች እና የመንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የመንግስት ግዥን በዕቅድ ላይ በተመሠረተና ገንዘብ ሊያስገኝ የሚችለውን ከፍተኛ ጥቅም /Value for Money/ ማስገኘት በሚያስችል መልኩ መፈፀም እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ 
ተቋማት የመንግስትና የህዝብ ኃብት የሆኑትን ንብረቶች በአግባቡ ይዘው ሊያስተዳድሩና አገልግሎት ላይ ሊያውሉ እንደሚገባም በምክክር መድረኩ ላይ ጠቅሰዋል፡፡ 
ዶ/ር ኢዮብ በውይይቱ ላይ እንደገለፁት ተቋማት ጊዜያቸው ያለፈባቸው ንብረቶች ለበለጠ ጉዳት ከመዳረጋቸው፣ በሰውና በአካባቢ ላይ ጉዳት ከማድረሳቸው አስቀድሞ መንግስት በዘረጋው የአወጋገድ ሥርዓት መሠረት ሊያስወግዱ እንደሚገባ አሰረድተዋል፡፡ 
የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጄንሲ የፌደራል ባለበጀት ተቋማት የግዢና የንብረት አስተዳደር ስርዓታቸውን ለማሻሻል፣ በብቃትና በቅልጥፍና እንዲወጡ ለማስቻል በየደረጃው ላሉ ኃለፊዎችና ባለሙያዎች በርካታ የአጭርና የረዥም ጊዜ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎችን እየሰጠ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በአብዛኛው የፌዴራል ባለበጀት መ/ቤቶች እና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያለው የግዥ አፈፃፀምና የንብረት አስተዳደር በርካታ ችግሮች የሚስተዋሉበት፣ እንዲሁም ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ የፈሰሰባቸው የመንግሥት ንብረቶች ለብክነት እየተጋለጡ መሆናቸውን በኦዲትና በሱፐርቪዥን ስራዎች መረጋገጡን የገንዘብ ሚኒስቴር  ዴኤታው ገልፀዋል፡፡
በዘርፉ ላይ የሚታየውን ችግር በኤጀንሲው አቅም ብቻ የሚፈታ ባለመሆኑ የምክክር መድረኩ አስፈልጓል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው በጋራ መምከርና በአሠራር ሂደት እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን መለየት፣ የመፍትሔ ሀሳቦችን ማመንጨት እና ቀጣይ አቅጣጫዎችን በጋራ ማስቀመጥ የግድ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በምክክር መድረኩ ላይ በዘላቂና በአረንጓዴ የግዢ ስርዓት ዙሪያ ላይ ሙያዊ ማብራሪያ የሰጡት  ከሲቪል ሰርቪስ ዩንቨርሲቲ ዶ/ርታዲዎስ መንታ ሲሆኑ የዘላቂ እና የአርንጓዴ ግዢ ገንዘብ ሊያስገኝ የሚችለውን ከፍተኛ ጥቅም የሚያረጋግጥ፣ ውጤታማ የሃብት አጠቃቀም፣የበካይ ልቀትን የሚቀንስና ዘላቂ ልማትን የሚያረጋግጥ መሆኑ እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡
በመድረኩም የገንዘብ ሚኒስቴር፣ የገቢዎች ሚኒስቴር፣ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር፣ የመከላከያ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ፣ የግብርና ሚኒስቴር፣ የማኅበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ፣ የትምህርት ሚኒስቴርን ጨምሮ 35 የፌዴራል ተቋማት ተሳታፊዎች ሆነዋል።

2426 Views