የትምህርት ሚኒስቴር፣ የተጠሪ ተቋማትና የ47 ዩኒቨርስቲዎች የ2016 በጀት ስሚ መርሀ ግብር ተከናወነ፡፡

May 2, 2023

ሚያዚያ 24 / 2015 ዓ.ም - የትምርህት ሚኒስቴር፣ የተጠሪ ተቋማትና የ47 የመንግስት ዩኒቨርስቲዎች የ2016 በጀት ስሚ መርሀ ግብር በገንዘብ ሚኒስቴር የመሰብሰቢያ አዳራሽ ተካሄደ፡፡

የበጀት ስሚ ፕሮግራሙን የመሩት የገንዘብ ሚኒስትሩ ክቡር አቶ አህመድ ሺዴ የበጀት ስሚውን ሲያስጀምሩ እንደገለጹት የመንግስትን በጀት በአግባቡና በቁጠባ ውጤት በሚያመጣ መልኩ መጠቀም የ2016 በጀት አመት  አቅጣጫ መሆኑን ጠቁመው ባለበጀት የመንግስት መስሪያ ቤቶች ከገንዘብ ሚኒስቴር በተሰጣቸው የበጀት ጣሪያና የመንግስትን የፋናስ አቅም ባገናዘበ መልኩ የ2016 በጀታቸውን ማዘጋጀት አንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

በተለይም ዩኒቨርስቲዎች የእውቀትና የምርምር ማእከላት በመሆናቸውን በበጀት አመዳደብ ትኩረት የተሰጣቸው መሆናቸውን ክቡር ሚኒስትሩ አመልክተው ዩኒቨርስቲዎቹ የሚመደብላቸውን በጀት ፈጠራ በታከለበትና የቁጠባ ስርአት በመዘርጋት መጠቀም ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ኢዮብ ተካልኝ በበኩላቸው እንደገለጹት በበጀት አጠቃቀም ረገድ ሀገራዊ እይታ እንደሚያስፈልግና በሀገር ደረጃ የጀመርናቸውን ፕሮጀክቶት አንዴት እንጨርሳለን የሚለውን ታሳቢ አድርገን መስራት እንዳለብን አመልክተው በ2016 በጀት አመት ከዚህ ቀደም የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን መጠናቀቅ ያለባቸውን ቅድሚያ በማውጣት ለማጠናቅቅ ጥረት ማድረግ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ በበጀት ግምገማው ወቅት እንደገለጹትም የትምህርት ሚኒስቴር የሀገሪቱን የትምህርት ጥራት ለማስጠበቅ የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገ መሆኑን አመለክተው የትምህረት ጥራትን ለማስጠበቅ አንዱ ግብአት የሆነውን የመጻህፍት ህትመት ለማከናወን እንዲሁም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናን በዩኒቨርስቲዎች ውስጥ ለመስጠት ከፍተኛ ወጪን የሚጠይቅ በመሆኑ ከልማት አጋሮች ከሚገኘው ድጋፍ በተጨማሪም ገንዘብ ሚኒስቴርም የበጀት ድጋፍ እነዲያደርግ በባለሙያዎች ደረጃ ተጨማሪ ምክክር እነደሚያስፈልግም አሳስበዋል፡፡

በበጀት ስሚ ፕሮግራሙ ከተሳተፉት 47 ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ ለአ/አ፣ ለኮተቤ፣ ለአክሱም፣ ለወሎ፣ ለአዳማ፣ ለአርባምንጭና ለመቱ ዩኒቨረስቲዎች እድል ተሰጥቶ ከበጀት ዝግጅት አንጻር የዩኒቨርስቲዎቹን ልዩ ሁኔታ አቅርበው ውይይት የተካሄደበት ሲሆን በገንዘብ ሚኒስቴር ከተሰጣቸው የበጀት ጣሪያ በላይ ያቀረቡ ዩኒቨርስቲዎች እስከ ሚያዚያ 30 / 2015 ዓ.ም ድረስ የ2016 በጀታቸውን አስተካከክለው እንዲያቀርቡ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡

በተመሳሳይ መልኩ የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር፣ የፕላንና ልማት ሚኒስቴርና የተጠሪ ተቋማት የ2016 በጀት እቅድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡

744 Views