የነጩ ፖስታ ጎርፍ ለነጩ ቤተ መንግስት ሀገራዊ ንቅናቄ በገንዘብ ሚኒስቴር ተጀመረ

Sept. 22, 2021

መስከረም 12 2014 ዓ.ም ፡- የነጩ ፖስታ ጎርፍ ለነጩ ቤተ መንግስት ሀገራዊ ንቅናቄ የገንዘብ ሚኒስቴርና የተጠሪ መስሪያ ቤቶች አመራሮችና ሰራተኞች በተገኙበት በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መሰብሰቢያ አዳራሽ ዛሬ ተጀመረ፡፡

በሀገራዊ ንቅናቄው ማስጀመሪያ ስነ ስርአት ላይ የተገኙት የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው ክቡር ዶ/ር ኢዮብ ተካሊኝ እንደገለጹት ይህ “የነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተ-መንግስት” በሚል መሪ ቃል የሚካሄደው ሀገራዊ ንቅናቄ አላማ የኢትዮጵያውያን እውነታ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ማሳወቅ፣ የአሸባሪውን ህወሓት አገር የማፍረስ ወረራ ማጋለጥ፣ በሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሰራዊት ላይ አሸባሪው ህወሓት የፈጸመውን ግፍ ማሳየት፣ አሸባሪው ቡድን በአማራና በአፋር ክልሎች በፈጸመው ወረራ በሚሊዮን በሚቆጠሩ ዜጎች ላይ ያስከተለውን የህይወትና የንብረት ጉዳት ይፋ ማድርግና ሌሎች ቡድኑ የሚፈጽማቸውን ኢሰብአዊ ድርጊቶችንና የሀሰት ፕሮፓጋንዳዎችን ማጋለጥ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በንቅናቄው ከአምስት ሚሊዮን በላይ ወጣቶችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ፊርማቸውን በማሰባሰብ የነጭ ፖስታ ጎርፍ ወደ አሜሪካው ነጩ ቤተ መንግስት እንደሚላክ ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው ተቅሰው በአሁኑ ወቅት በመላ  ሀገሪቱ ዜጎች አለም አቀፉ ማህበረሰብ የኢትዮጵያን እውነታ እንዲረዳ፣ ከአጉል ጣልቃ ገብነት እንዲታቀብና የሕወሓትን ትክክለኛ ገጽታ እንዲረዳ ፊርማቸውን በማኖር ላይ  መሆናቸውንም ጨምረው ገልጸዋል።

በዚህ ሀገራዊ ንቅናቄ የገንዘብ ሚኒስቴርና የተጠሪ ተቋማት ሰራተኞችና አመራሮችም የኢትዮጵያን እውነታ ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማሳወቅና የአሸባሪውን ሕወሓት እኩይ ተግባር ለማጋለጥ በሚደረገው ሀገራዊና ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉም ሚኒስትር ዴኤታው ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

1534 Views