የአለም ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ለኢትዮጵያ የ745 ሚሊዮን ዶላር የፋይናንስ ድጋፍ አጸደቀ

Dec. 15, 2022

ታህሣሥ 6 / 2015 ዓ.ም - የአለም ባንክ የስራ አስፈጻሚ ዳይሬክተሮች ቦርድ በኢትዮጵያ ለመሰረታዊ የጤና አገልግሎትና ለጎርፍ ጉዳትን መከላከያ ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ የሚውል የ745 ሚሊዮን ዶላር የፋይናንስ ድጋፍ አጸደቀ፡፡ 

ለመሰረታዊ የጤና አገልግሎት ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ 445 ሚሊዮን ዶላር የተመደበ ሲሆን ፕሮጀክቱ በመላ ኢትዮጵያ መሰረታዊ የጤና አገልግሎት ለማዳራስ ያለመ ሲሆን በተለይም በስነ ተዋልዶ ጤና፣  በእናቶችና ህጻናት ጤና እንዲሁም በስነ ምግብ አገልግሎት ላይ ትኩረት የሚያደርግ ነው፡፡

የመሰረታዊ ጤና አገልግሎት ፕሮጀክቱ በግጭት ለተጎዱ አካባቢዎች ቅድሚያ የሚሰጥ ሲሆን በግጭቱ ከሌላው የህብረተሰብ ክፍል  ይልቅ ሴቶችና ህጻናት ይበልጥ ተጋላጭ በመሆናቸው ለነሱ ይበልጥ ትኩረት እንደሚሰጥም ታውቋል፡፡

ለጎርፍ ጉዳት መከላከያ ፕሮጀክት ደግሞ 300 ሚሊዮን ዶላር የተመደበ ሲሆን ፕሮጀክቱ በጎርፍና በሌሎች የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ለሚያጋጥሙ የተፈጥሮ አደጋዎች ለመከላከል የሚውል ሲሆን ፕሮጀክቱ በአዋሽ፣ በኦሞና በስምጥ ሸለቆ ተፋሰሶች የሚኖሩ የማህበረሰብ ክፍሎችን ጨምሮ በጎርፍና በአየር ንብረት ለውጥ ጉዳት የሚደርስባቸውን ሌሎች  የማህበረሰብ ክፍሎች  ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡

በአለም ባንክ ጥናት መሰረት እ.ኤ.አ በ2020 የጎርፍ መጥለቅለቅ በኢትዮጵያ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ህዝብ ላይ ጉዳት ማድረሱንና ከ300 መቶ ሺ በላይ ሰዎችን ያፈናቀለ ሲሆን 358 ሚለዮን ዶላር የሚገመት ጉዳት ማድረሱ ታውቋል፡፡

1873 Views