የአዋሽ ወንዝ በአፋር ክልል እና በአጎራባች ክልሎች የሚያስከትለውን የጎርፍ አደጋ በተመለከተ በገንዘብ ሚኒስቴር ውይይት ተካሄደ
March 9, 2021
የገንዘብ ሚኒስትር ክቡር አቶ አህመድ ሽዴ ከአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳደር ከክቡር አቶ አወል አርባ ጋር የአዋሽ ወንዝ የሚያስከትለውን የጎርፍ አደጋን በመከላከልና በመቆጣጠር ላይ ያተኮረ ውይይት ዛሬ የካቲት 10/2013 ዓ.ም በሚኒስቴሩ ጽ/ቤት አካሄዱ፡፡
ክቡር ሚኒስትሩና የክልሉ ርእሰ መስተዳድር የአዋሽ ወንዝ ቀደም ባሉት ዓመታት በተደጋጋሚ ጊዚያት በከፍተኛ ሁኔታ በመሙላት በአካባቢው ነዋሪዎች፣ በቁም እንስሳት እና በንብረት ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ እየተሰሩ ባሉ ስራዎች ላይ ተወያይተዋል፡፡
ችግሩን ለመከላከል ክልሉ ከፌዴራል መንግስት እና ከልማት አጋሮች ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ መሆኑን ክቡር አቶ አወል አርባ አመልክተው፣ ከዚህ ቀደም ጉዳቱ የደረሰባቸውን ነዋሪዎች በዘላቂነት የማቋቋም ስራዎችም መልካም ውጤት እንዳስገኙ አስረድተዋል፡፡
ክቡር አቶ አህመድ በበኩላቸው የአዋሽ ወንዝ በተደጋጋሚ ጊዚያት የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ የቅድመ መከላከል ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበው የፌዴራል መንግስት ከክልሉ ጋር በመተባበር ከአዋሽ ወንዝ ጋር በተያያዘ የሚደርሰውን የጎርፍ አደጋ ለመከላከል አስፈላጊው ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርግ አመልክተዋል፡፡