የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት የገንዘብ ሚኒስትሮች በቀጠናዊ ትብብርና የአካባቢውን የልማት ስራዎች ላይ ውይይት አካሄዱ
March 31, 2021
በቪዲዮ ኮንፍረንስ በተካሄደው የገንዘብ ሚኒስትሮች የጋራ ስብሰባ በዋንኛነት የአካባቢውን ልማት ለማጎልበትና በቀጠናው እየተስተዋሉ ያሉ ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን በመቅረፍ ላይ ያተኮረ ውይይት አካሄዱ፡፡
ቀጠናውን በአሁኑ ወቅት እየፈተኑ የሚገኙ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች በተለይም የኮሮና ወረርሽኝ ያስከተለውን የምጣኔ ሀብት ቀውስና የበረሃ አንበጣ በግብርና እና በምግብ ዋስትና ላይ ያሳደረውን አሉታዊ ተፅዕኖ ለመፍታት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ውይይት አድርገዋል፡፡
በውይይቱ ላይ የተሳተፋት የኢትዮጵያ የገንዘብ ሚኒስትር ክቡር አቶ አህመድ ሽዴ የኮሮና ወረርሽኝ በተለይም ዝቅተኛ ምጣኔ ሀብት ባላቸው የአፍሪካ ሀገራት ላይ በኢኮኖሚና በማህበራዊ መስኮች ላይ ከፍተኛ ጫና አሳድሯል ብለዋል፡፡ በአፍሪካ ቀንድ የሚገኙ ሀገራትም በወረርሽኙ ጉዳት የተነሳ ያለባቸውን የውጭ ዕዳ ወቅቱን ጠብቀው መክፈል አለመቻላቸው እና ሁኔታውም ከዚህ የበለጠ የከፋ ሰብኣዊ ቀውስ እንዳይከሰት ሀገራቱ በትብብር ሊሰሩ ይገባል ሲሉ ገልፀዋል፡፡
ሀገራት ከወረርሺኙ ተፅዕኖ ማገገም እንዲችሉም ደህንነቱ የተጠበቀ ውጤታማና በስፋት ሊገኝ የሚችል የኮቪድ 19 ክትባት በፍጥነት ማግኘትና ማሰማራጨት ይገባል ብለዋል፡፡
አቶ አህመድ አክልውም የቀጠናውን የኢኮኖሚ ውህደት እውን ለማድረግ በአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ ሴክሬታሪያት የመጀመሪያ ዓመት የሥራ ዘመን የተገኙ ውጤቶች እንዳይሸረሸሩ እየገጠሙን ያሉ ተግዳሮቶች እና ድንበር ተሻጋሪ ችግሮችን በብቃት ለመፍታት እስከአሁን ያሉ የትብብር ስልቶችን እንደገና ለማጤን እና አጋርነታችንን ለማጠንከር ይበልጥ መስራት ይገባል ሲሉም አስረድተዋል፡፡ በፅህፈት ቤቱ አስተባበሪነት እስከአሁን ከተመዘገቡት ውጤቶች መካከል በተምሳሌትነት በንግድ ውህደት ላይ የቀረበውን የፖሊሲ እርምጃዎች አንስተዋል ፡፡
በውይይቱ ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ የጅቡቲ፣የኬንያ፣ሶማሊያ፣ኤርትራና ሱዳን የገንዘብና የልማት ሚኒስትሮች ተሳትፈዋል፡፡