የኢትዮጵያና የኔዘርላድ መንግስታት በግብርና እና በኢንደስትሪ ዘርፍ የሚያደርጉትን ኢኮኖሚያዊ ትብብር ማሳደግ እንደሚያስፈልግ ተነገረ
March 15, 2022
መጋቢት 5 / 2014 ዓ.ም - የኔዘርላንድ መንግስት እየሰጠ በሚገኘው የልማት ትብብር ድጋፍ፣ በኢትዮጵያ የግብርናን አቅም በማሳደግና በአግሮ ኢንዱስትሪ በተለይም በወተት ተዋጽኦና በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት በርካታ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረጉን የገንዘብ ሚኒስቴር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ ሰመሬታ ሰዋሰው ገለጹ፡፡
ክብርት ሚኒስትሯ ከግብርና ሚኒስቴር ከፍተኛ የስራ አመራሮች ፣ከኔዘርላንድ ኤምባሲና ከኔዘርላንድ የልማት ደርጅት ሀላፊዎች ጋር በመሆን በዱከም፣ በቢሾፍቱና በሞጆ አካባቢ በኔዘርላንድ የልማት ድርጅትና በኔዘርላንድ ኢንቨስተሮች እየተከናወኑ ያሉ የአግሮ ኢንዱስትሪና የአትክልትና ፍራፍሬ ልማቶችን በጎበኙበት ወቅት እንደተናገሩት የኔዘርላነድ መንግስት፣ የኔዘርላንድ የልማት ድርጅትና ኢንቨስተሮች በአካባቢውና በመላ ሀገሪቱ የሚያከናውኗቸው የልማት ስራዎች በተቀናጀ ሁኔታ በመመራታቸው ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል ከመፍጠራቸውም በላይ የገበያ ትስስር በመፍጠር የወተት ተዋጽኦና የአትክልትና ፍራፍሬ አምራቾች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻላቸውን እንዲሁም የምግብ ዋስትና በማረጋገጥ ረገድ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን አመልክተዋል፡፡
በኢትዮጵያ የኔዘርላንድ ኤምባሲ ምክትል አምባሳደር ሚስተር ቲጅስ ውድስታር የኢትዮጰያና የኔዘርላንድ ኢኮኖሚያዊ ትብብር ረጅም አመታትን የስቆጠረ መሆኑንና ኔዘርላንድ በኢትዮጵያ 10ኛ ትልቋ ኢንቨስተር መሆኗን ጠቁመው የኔዘርላንድ የልማት ድርጅትና የኔዘርላንድ ኢንቨስተሮች በተለይ በአግሮ ኢንደስትሪ፣ በወተት ተዋጽኦና በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ዘርፍ ውጤታማ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
በመስክ ምልከታው በኔዘርላንድ የልማት ድርጅት የገንዘብና የቴክኒክ ድጋፍ በአቮካዶ ችግኝ ልማትና በወተት ተዋጽኦ ልማት የተሰማሩ ሴቶች የደረሱበት ደረጃ የተጎበኘ ሲሆን በሚሰሩትም ስራ ውጤታማ መሆናቸውንና ኑራቸውም እየተሻሻለ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡
የኔዘርላንድ ባለሀብቶች ንብረት የሆነውና በቢሾፍቱ ከተማ የሚገኘው ‹‹ ሆላንድ ዴይሪ›› የተሰኘው በወተትና በእርጎ ምርት የሚታወቀው ፋብሪካ በልኡካን ቡድኑ የተጎበኘ ሲሆን ኢንዱስትሪው መቶ በመቶ ጥራት ያለውን የወተት ምርት የሚያገኘው ባካባቢው ካሉ አነስተኛና መካከለኛ የወተት ላም አርቢዎች መሆኑን የፋብሪካው ስራስኪያጅ አመልክተው የታሸገ የወተትና የእርጎ ምርታቸውን በመላው ኢትዮጵያ በሚገኙ ሱፐር ማርኬቶች እንደሚያከፋፍሉና ለ163 ዜጎችም የስራ እንድል እንደፈጠሩ አስረድተዋል፡፡
በምስራቅ ሸዋ ዞን ኤጄርሳ ወረዳ የሚገኘው ‹‹ ፍሎርነሲስ አቢሲኒያ›› የአትክልትና ፍራፍሬ አምራች ሌላው የተጎበኘው የኔዘርላንድ ባለሀብቶች የአግሮ ኢንደስት ልማት ሲሆን ይህ ተቋም የተለያዩ የአበባ ዝርያዎችን ወደ አውሮፓ በመላክ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኝና ለበርካታ ዜጎችም የስራ እድል የፈጠረ መሆኑን ተመልክቷል፡፡
እነዚህ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ፣ የስራ እድል በመፍጠርና ከፍተኛ ገቢ በማስገኘት በሀገሪቱ ልማትና እድገት ላይ የላቀ አስተዋጽኦ በሚያበረክቱ አግሮ ኢንዱስትና የትክልትና ፍራፍሬ ልማት ዘርፎች የተሰማሩ አነስተኛና መካከለኛ አምራቾችና ባለሀብቶች በስራ ሂደት የገጠሟቸውን ችግሮች ለልኡካን ቡድኑ የገለጹ ሲሆን መንግስት ከልማት አጋሮች ጋር በመተባበር ችግሮችን ደረጃ በደረጃ በመቅረፍ ለአምራቾችና ለኢንቨስተሮች ምቹ ሁኔታ በመፍጠት ነባር ኢንቨስተሮችን ለማበረታታና አዳዲስ ወደ ኢንዱስትሪው በመግባት ላይ ያሉትን ኢንቨሰተሮች ለመደገፍ ጠንክሮ እንደሚሰራ የገንዘብ ሚኒስቴር የኢኮኖሚ ትብብር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ ሰመሬታ ሰዋሰው አረጋግጠዋል፡፡