የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳን ማሳካት ምን ያህል አስፈላጊ ነው?

May 21, 2021

ኢትዮጵያ ባለፉት አስር አመታት በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በሰው ሀብት ልማት ዘርፎች ዋና ዋና መሻሻሎች አሳክታለች፡፡ እነዚህ ስኬቶች ግን በግሉ ዘርፍ መቀጨጭና በማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት የታጀቡ ነበሩ፡፡ ይባስ ብሎ ደግሞ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ መከሰት ኢኮኖሚውን በሀገር አቀፍና አለም አቀፍ ደረጃ ጎድቶታል፡፡ ስለዚህም እነዚህን ኢኮኖሚያዊ ተግዳሮቶችን ለመቋቋም ኢትዮጵያ ትከተለው የነበረውን አቅጣጫ በመፈተሸ ተከታይነት ያላቸውን ዘላቂ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን መቅረጽ ነበረባት፡፡

ኢትዮጵያ ቀድሞ ትከተለው የነበረው  በመንግስት ይከናወን የነበረው የተጋነነ የልማት ስራ ደካማ የፕሮጀክት አፈጻጸምና ዝቅተኛ የውጭ ንግድ ታክሎበት አጠቃላይ የኢኮኖሚ አፈጻጸሙን በችግር የተተበተበ እንዲሆን አድጎታል፡፡ በመሆኑም መንግስት ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ ቀርጾ ተግባራዊ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ማሻሻያው የኢኮኖሚ ዘርፎችንና መዋቅራዊ ሽግግሮችን ያካተተ ሲሆን የንግድ ማነቆዎችን ለማስወገድ፣ ለውጭ ባለሀብቶች ተሳትፎና ውድድር ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር የሚያግዝ፣ የግሉ ዘርፍ በሀገሪቱ ልማትና እድገት ላይ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርግ እንዲሁም የመንግስት የልማት ድርጅቶችን አሰራር ግልጽና ተጠያቂነት የሰፈነበት እነዲሆን የሚያስችል ነው፡፡

በዚህ ፈታኝ ወቅት ለግሉ ዘርፍ ምቹ ምህዳር በመፍጠር፣ የውጭ ንግድን ለማሳደግ ጥረት በማድረግ፣ ምርታማነትንና የአገልግሎት አሰጣጥን በማሻሻል፣ የማህበረሰብ አገልግሎት ከለላን በማጎልበት በአጠቃላይ መዋቅራዊ ማሻሻያ በማድረግ ማክሮ ኢኮኖሚው ጤነኛ እንዲሆን ጥረት በመደረግ ላይ ይገኛል፡፡

የመዋቅራዊ ሽግግሩ የመጨረሻ ግብ ለሰፊው የሀገሪቱ ወጣት የስራ እድል መፈጠር መሆኑ እሙን ነው፡፡ ፍትሀዊ የሀብት ክፍፍል ያለመኖር በ2010 ዓ.ም የመንግስት ለውጥ ማስከተሉን ልብ ይሏል፡፡ ይህን ችግር ለዘለቄታው መፍታት የሀገሪቱንና የቀጠናውን ሰላምና መረጋጋት እውን ማድረግ ነው፡፡

የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው አፈጻጸም የመጀመሪያው ወቅት አፈጻጸም ግምገማ በተለይም ትክክኛውን የፖሊሲ አቅጣጫ ከመቅረጽና አስቻይ አሰራሮችን ተግባራዊ ከማድረግ አኳያ አበራታች ውጤት ተመዝግቧል፡፡ ማሻሻያውን ተግባረዊ ማድረግና ማጎልበት ከረጅም ጊዜ አኳያ በልማታችንና በእድገታችን ላይ አወንታዊ ሚና የሚጫወት ሲሆን ማሻሻያውም ትርጉም ያለው ለውጥ እንደሚያመጣ እሙን ነው፡፡

እንዲህም ሆኖ ግን ሁሉን አሳክተናል ብለን እጆቻችንን አጣምረን የምንቀመጥበትና በስኬቶቻችን ረክተን የምንዝናናበት ወቅት ላይ አይደለንም፡፡ አርቀን በማየት በስኬቶቻችን ላይ በመጨመርና ይበልጥ በመትጋት ለሀገራችን ልማት፣ እድገት እንዲሆም ሰላምና ደህንነት ጠንክረን የምነሰራበት ታሪካዊ ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡

መንግስት ትክክለኛውን የልማትና የእድገት ፖሊሲ መቅረጽ የመጀመሪያው የእድገት ጎዳና መግቢያ መሆኑን ያጤናል፡፡ ማሻሻያዎቹንና ፖሊሲዎቹን በተሳካ ሁኔታ ተግባረዊ ለማድረግ የነቃና አላማውን ከግብ ለማድረስ ሁኔታዎች የተመቻቹለትና አቅሙ የጎለበት የመንግስት ሰራተኛ እንደሚያስፈልግም ልብ ይሏል፡፡ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በሀገሪቱ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ህይወት ላይ የደቀነብንን አደጋ በመታገል፣ የግሉ ዘርፍ በአገር ኢኮኖሚ ግንባታ ያለውን የማይተካ ሚና በማጤንና የስራ ፈጣሪነቱን አቅም ከግምት በማስገባት ለሀገሪቱ ሁለንተናዊ ልማት፣ እድገትና ደህንነት መትጋት ይጠበቅብናል፡፡

 

3239 Views