የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የማሻሻያ ስራዎች ቀጣይነታቸው እንዲረጋገጥ በትኩረት መሰራት እንደሚያስፈልግ ተገለፀ
March 9, 2021የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ባለፉት ስድስት ወራት ያከናወናቸው ዋና ዋና የማሻሻያ ስራዎች የባንኩን ትርፋማነት ለማሳደግ እንዳስቻሉ ተገለፀ፡፡
በገንዘብ ሚኒስትር በክቡር አቶ አህመድ ሽዴ በተመራ ግምገማ ላይ እንደተገለጸው ባንኩ ትርፋማነቱ ከባለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በብር 304.16ሚሊየን ብልጫ ማለትም በ150 በመቶ ከፍ ያለሆኖ ተገኝቷል፡፡
አቶ አህመድ ሽዴ የባንኩ ትርፋማነት የተገኘው ተለያዩ የለውጥ ስራዎች በመተግበራቸው እንደሆነ በግምገማው ወቅት አብራርተዋል:: በተለይም ባንኩ የነበረውን ብድር የማስተዳደርና የመቆጣጠር አቅም ማሳደጉ ለዚህ ውጤት እንዳበቃው ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም የኢትዮጵያ የልማት ባንክ በስድስት ወር ውስጥ የህዳሴ ግድብ ቁጠባን በተመለከተ ብር 500 ሚሊየን ለመፈፀም አቅዶ ብር 883.47 ሚሊየን ለመሰበብሰብ መቻሉ የሚበረታታ መሆኑን መሆኑ በግምገማው ተመልክቷል፡፡ በተለይም ኢትዮጵያዊያን በራሳቸው አቅም እየገነቡት ያለው የህዳሴ ግድብ ወቅቱን ጠብቆ ማጠናቀቅ እንዲቻል ባንኩ ጥረቱን አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባው ክቡር አቶ አህመድ ሽዴ አሳስበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የማሻሻያ ስራዎች ውጤታማነታቸው ቀጣይ ለማድረግ ባንኩ በአዳዲስ እና በቴክኖሎጂ የታገዙ የአሰራር ስርዓቶችን ማጎልበት በግምገማው መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡
የባንኩን የውጭ ምንዛሬ አቅም ለማሳደግ እና የባንኩን አማራጭ የሀብት ምንጭ ለማጎልበት የሚያስችሉ ተግባራት ቀዳሚ ትኩረት የሚሹ መሆናቸውን አቶ አህመድ ሽዴ አስረድተው፣ ባንኩን በዘላቂነት ከሀብት ጥገኝነት ለማውጣት የማሻሻያ ስራዎች በወጣላቸው መርሀ ግብር መሰረት መተግበር እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል፡፡