የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባለፉት ስድስት ወራት ከ58 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱ ተገለጸ፡፡

March 3, 2022

የካቲት 22 2014 ዓ.ም - የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የግማሽ አመት የስራ አፈጻጸም በገንዘብ ሚኒስቴርና በመንግስት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳር በሂልትን ሆቴል በተገመገመበት ወቅት እንደተገለጸው ባንኩ ከሀምሌ 2013 እስከ ታህሳስ 2014 ዓ.ም ባሉት ስድሰት ወራት ውስጥ 58.1 ቢሊዮን ብር ገቢ አግኝቷል፡፡

ይህ የባንኩ የገቢ አፈጻጸም ከእቅዱ ጋር ሲነጻጸር 136 በመቶ ሲሆን ከውጭ ምንዛሪ ግኝት አንጻርም በግማሽ አመቱ 1.4 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት አቅዶ 1.26 ቢሊዮን ዶላር ማግኘቱንና ይህም የእቅዱ 84.4 በመቶ መሆኑ ታወቋል፡፡

የባንኩ ጠቅላላ የቁጠባ አፈጻጸም በግማሽ አመቱ 823 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን ይህም ከባለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ21 በመቶ ብልጫ እንዳለው በግምገማው ወቅት ከቀረበው ሪፖርት ለማወቅ ተችሏል፡፡

ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመቀጠል የግማሽ አመት የስራ አፈጻጸሙ የተገመገመው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የአሰራር ለውጥ በማድረጉና አመራር በመቀየሩ የነበሩበትን ድክመቶች አርሞ በለውጥ ጎዳና ላይ እንደሚገኝና ከፍተኛ መሻሻሎች እንደታዩበትም ለመረዳት ተችሏል፡፡

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ባለፉት ስድስት ወራት አብዛኛውን የሪፎርም እስትራቴጂ ስራዎች ተግባራዊ በማድረጉ፣ በብድር ማካካሻ የተያዙ ፕሮጀክቶች ተረከቦ ወደ ስራ እንዲገቡ በማስቻሉ፣ የባንኩን ቢዝነስ ሞዴል በማስተካከሉና የብድር አሰጣጥ ሥርዓቱ የሀገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ ያደረገ ማስተካከያ በማድረጉ የባንኩ የፋይናንስ ጤናማነት እየተሻሻለ መምጣቱም ተገልጿል፡፡

የግምገማ መድኩን የመሩት የገንዘብ ሚኒስትር ክቡር አቶ አህመድ ሺዴ የኢትጵያ ንግድ ባንክ የግሉን ዘርፍ የቁጠባ መጠንና የዲጂታል ባንኪንግ አገልግሎት ማሰደግ እንዳለበት ጠቁመው ጤናማ የፋይናንስ ስርአቱን አጠናክሮ ለመቀጠል በአዳዲስ ቴክኖሎጂ መታገዝና ተወዳደሪ ሆኖ መገኘት አንዳለበት አሳስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ አመራሮች በአዳዲስ እንዲተኩ ከተደረገ በኋላ በረካታ ለውጦች የተመዘገበና ብድር የማሰተዳደር እንዲሁም የክትትል አቅምና ልምዱ እያደገ መሄድ እንደቻለ ክቡር አቶ አህመድ አመልክተው ባንኩ ያለበትን የሰው ሃይል ችግር ግን በቀጣይ ትኩረት ሰጥቶ መፍታት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

822 Views