የኢትዮጵያ የሒሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ በኦዲት ጥራት ማረጋገጥና በኦዲት ግኝቶች ላይ ከባለድረሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ አካሄደ
Dec. 7, 2022
ህዳር 28 / 2015 ዓ.ም - የኢትዮጵያ የሒሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ የኦዲት ሙያ አገልግሎት ከሚሰጡ የተመሰከረላቸው የኦዲት ድርጅት ባለቤቶችና ባለሙያዎች ጋር በኦዲት ጥራት ማረጋገጥና በኦዲት ምርመራዎች ግኝቶች ላይ የምክክር መድረክ አካሄደ፡፡
ከቦርዱ ፍቃድ ወስደው የኦዲት ሙያ አገልግሎት የሚሰጡ ከ150 በላይ የኦዲት ድርጅት ባለቤቶችና ባለሙያዎች የተሳተፉበትንና ከህዳር 27 - 28 ቀን 2015 ዓ.ም የተካሄደውን የምክክር መድርክ የመሩት የቦርዱ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሂክመት አብደላ እንደተናገሩት የኦዲት ጥራት ማረጋገጥና ምርመራዎች ማደረግ ከተጀመረ አንድ ዓመት ያሰቆጠረ መሆኑን ጠቅሰው ቦርዱ የኦዲት ድርጅት ባለቤቶችንና ባለሞያዎችን የኦዲት ጥራትን ለማሳደግ ያስችል ዘንድ በቦርዱ የተዘጋጀው የኦዲት ማንዋል ለሁሉም እንዲደርሳቸው ተደርጎል በኦዲት ማንዋል እና በኦዲት ደረጃዎች ላይ ስልጠናዎች መስጠቱን አስረድተዋል፡፡ የኦዲት ጥራት ምርመራ ውጤትን በተመለከተም በቅርብ ይፋ እንደሚደረግ ዋና ዳይሬክተሯ ጨምረው ገልጸዋል፡፡
በአለም አቀፍ ደረጃ በኦዲት ስራዎች ላይ ሀገራት ብዙ ትኩረት ሰጥተው እየሰሩበት መሆኑንም ወ/ሮ ሂክመት ጠቅሰው ቦርዱ የራሱን አቅም ለመገንባትም እ.ኤ.አ በ2022 በአለም አቀፍ ደረጃ በተካሄደው የኦዲት ጉባኤ የኢትዮጵያ የልዑካን ቡድንን በመምራት ባደረገው ተሳትፎ የኦዲት ጥራትን በተመለከተ ከተለየዩ ሀገራት ጋር የልምድ ልውውጦችን ማካሄድ መቻሉንና በተለይም የፓን አፍሪካ የሂሳብ ባለሙያዎች ፌዴሬሽን እየተጠናከረ መምጣት ጥራት ያላቸው የኦዴት ደረጃዎችንና መመዘኛዎች እንዲገኙ ማስቻሉን አብራተዋል፡፡
ቦርዱ በፌዴራል ደረጃ ከሚያደርገው አስተዋጽኦ በተጨማሪም በክልሎች ለሚገኙ የሒሳብና ኦዲት ባለሙያዎች የሙያ ፈቃድ በመስጠት፣ የሒሳብ ሙያ ማህበራት ምዝገባ እና ፈቃድ እንዲያገኙ በማድርገ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰው በአንዳንድ ክልሎች ላይ የኢትዮጵያ የሒሳብ አያያዝ እና ኦዲት ቦርድ ፈቃድ እንደተሰጣቸው በማስመሰልና ሐሰተኛ ሰነዶች በመጠቅም የኦዲት ሰራዎች እየሰሩ በመሆኑ ቦርዱ በዚህ አይነት ህገ ወጥ ተግባራት ላይ በተሰማሩ ማህበራትና ባለሞያዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ እየወሰደ እንደሚገኝ ጨምረው አስረድተዋል፡፡
እነዚህን ህገወጦች ለመከላከልና ተጠያቂ ለማድረግ ያስችል ዘንድ በቦርዱ የጥቆማ መቀበያ አጭር ኮድ 6773 ወይም ስልክ ቁጥር +251111541235 ላይ በመደወል ማህበረሰቡ ጥቆማ እንዲሰጣው ዋና ዳይሬክተሯ ጥሪ አስተላፈዋል፡፡
የኢትዮጵያ የሒሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ተጠሪነታቸው ለገንዘብ ሚኒስቴር ከሆኑት አራት የፌዴራል ተቋማት ውስጥ አንዱ መሆኑ ይታወሳል፡፡