የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት አገልግሎቱን በማዘመን ለዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ እራሱን እያዘጋጀ መሆኑ ተጠቆመ
March 9, 2021
በገንዘብ ሚኒስቴር በተካሄደው ስብሰባ የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት የግማሽ ዓመት አፈፃፀም ሪፖርት በቀረበበት ወቅት ድርጅቱ የማሻሻያ እርምጃዎችን በመውሰድ፣ ዘመናዊ አሰራሮችን በመከተል እና ውጪን በመቀነስ ትርፋማ መሆኑ ተገለፀ፡፡
በአፈፃፀም ግምገማው ላይ የተገኙት የገንዘብ ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታ ክብርት ያስሚን ወሀብራቢ እንዳሉት የተቋሙ የስራ እነቅስቃሴ መነቃቃት እያሳየ መምጣቱን የሚበረታታ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ አገልግሎቱንም በዘመናዊ አሰራር በማስደግፍ ተወዳዳሪና ኢትዮጵያ እያገነባች ላለችው ዲጂታል ኢኮኖሚ የበኩሉን አስተዋፅኦ እንዲያበረክት ተቋሙ በአዳዲስ በቴክኖሎጂዎች የታገዙ አገልግሎቶችን በማስተዋወቅ መስራት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታዋ እንዳሉት የተቋሙ ደንበኛች እርካታ ጥናት በማድረግ ችግሩን የመለየትና የመስተካከል ስራ መሰራት አለበትም ብለዋል፡፡ በጥናቱ ላይ ተመስርቶ ድርጅቱ አገልግሎቱ ፈጣን እና ቀልጣፋ አሰራሮችን በመዘርጋት የደበኞችን እርካታ ይበልጥ መጨመር እንደሚገባው ገልፀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ሀና አርአያስላሴ ተቋሙ በቀጣይ ከመደበኛው የመልዕክት አገልግሎት ማድረስ በተጨማሪ በኢ-ንግድና የተለያዩ የገንዘብ አገልግሎቶችን በስፋት በመስጠት ራሱን የማዘመን ስራ ላይ ትኩረት እድርጎ እየሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡