የእመርታ ቀን “እመርታ ለዘላቂ ከፍታ” በሚል መሪ ቃል በሳይንስ ሙዚየም ተከበረ
Published: Sept. 8, 2025
ጳጉሜ 3/ 2017 ዓ.ም - በገንዘብ ሚኒስቴር አስተባባሪነት ሌሎች ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችና የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ የተሳተፉበት የእመርታ ቀን “እመርታ ለዘላቂ ከፍታ” በሚል መሪ ቃል በሳይንስ ሙዚየም ተከበረ፡፡
መርሀ ግብሩን በንግግር የከፈቱት የገንዘብ ሚኒስትሩ ክቡር አቶ አህመድ ሺዴ እንደገለጹት ባለፉት ሰባት ዓመታት የተተገበሩ የለውጥ ሥራዎች አስተማማኝና ተወዳዳሪ ኢኮኖሚ እንዲገነባ መሠረት መጣላቸውን ጠቅሰው በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በማዕድን፣ በገቢ አሰባሰብና በሌሎችም ቁልፍ የልማት ዘርፎች ተጨባጭ ዕድገት መመዝገባቸውንና የታዩትም ለውጦች ኢትዮጵያ ከጥቂት ዓመታት በኋላ የምትደርስበትን ከፍታ የሚያመላክቱ መሆናቸውን አመልከዋል፡፡
እንደ ሀገር የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎረም ተግባራዊ በመደረጉ፣ በኢኮኖሚው የሚታዩ ተደራራቢ ችግሮችን በተለይም ዋጋ ግሽበትና የውጭ ምንዛሬ መዛብባትና አቅርቦት ችግሮችን በዘላቂነት እንዲፈቱ እጅግ አስፈላጊ ተግባራት መከነናወናቸውንና በዚህም ለእመርታችን መሰረት የሆኑ መልካም ውጤቶች እየታዩ መሆናቸውን አመልክተው በልማት እቅድና አስተዳደር አንድ እቅድ አንድ ሪፖርት በሚል መርሕ ፖሊሲዎች እንዲናበቡና እንዲቀናጁ እንዲሁም በቴክኖሎጂ የታገዘ ጠንካራ የክትትል ስርዓት በመዘርጋቱ የኢኮኖሚ ሪፎም ስራዎች ከልማታዊ ዘርፎች ሪፎርም ጋር እንዲቀናጁና እንዲተሳሰሩ አስችሏል ብለዋል፡፡
በመጨረሻም የእመርታን ቀን ስናከብር የሕዝባችንን ጥንካሬ፣ የለውጥ ፍሬዎችን እያጣጣምን ለወደፊቱ የተሻለ ጊዜና ለኢትዮጵያ ብልጽግና ተስፋ እንደምንሰንቅና ከሁሉም በላይ በቁርጠኝነት፣ በዲሲፕሊን እና በአንድነት መስራታችንን ከቀጠልን ወደፊቷን የበለጸገች ኢትዮጵያ የምናይበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም ብለዋል።
የእመርታ ቀንን ሰባት ተቋማት ማለትም ገንዘብ ሚኒስቴር፣ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ የገቢዎች ሚኒስቴር፣ የግብርና ሚኒስቴር፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እና የማዕድን ሚኒስቴር በጋራ አክብረዋል፡፡