የእዳና ሀብት አስተዳደር ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ተሾመለት
June 28, 2021
ለኮርፖሬሽኑ በምክትል ዋና ዳይሬክተርነት የተሸሙት አቶ ሙሉአለም ጌታሁን ሲሆኑ ኮርፖሬሽኑ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን የዕዳ ጫና በማቃለል ውጤታማ ሆነው እንዲዘልቁ የሚያግዝ አዲስ ተቋም ከመሆኑም በላይ የመንግስት የልማተ ድርጅቶችን ዕዳ በማቃለል በማክሮ ኢኮኖሚው ውስጥ የተፈጠረውን ያለመረጋጋት ለማስወገድ የሚያግዝ የመንግስት ድርጅት ነው፡፡
በ600 ቢሊዮን ብር መነሻ ካፒታል የተቋቋመው የዕዳና ሀብት አስተዳደር ኮርፖሬሽን ከፍትኛ የዕዳ ጫና ውስጥ የተዘፈቁ 7 የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ማለትም የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ሀይል ድርጅት፣ የኢትዮጵያ የኤልክትሪክ አገልግሎት፣ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ (የቀድሞው የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን)፣ የኬሚካል ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን፣ የኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን እና የኢትዮጵያ ስኳር ድርጅት እዳና ሀብት እንደሚያስተዳደር ታወቋል፡፡
ኮርፖሬሽኑ የንግድ ተቋም ቁመና የሚይዝ በመሆኑ እዳው በመንግስት በጀት ላይ ጫና እንደማይፈጥር የታመነበት ሲሆን የኮርፖሬሽኑ በንግድ ተቋምነት መመስረት ብቃት ያላቸውን አመራሮችና ባለሞያዎችን በመያዝ በገቢ ማስገኛ እንቅስቃሴዎች እንደሚሰማራም ታሳቢ ተደርጓል፡፡
መንግስት የልማት ድርጅቶቹ ውጤታማ ሆነው እንዲዘልቁና በሀገር እድገትና ልማት ላይ የበኩላቸውን አስተዋጽዖ እንዲያበረክቱ ሁል አቀፍ የማሻሻያ አጀንዳዎችን ቀርጾ ተግባራዊ ሲያደርግ የቆየ ከመሆኑም በላይ የኮርፖሬሽኑ መመስረት የልማት ድርጅቶቹ ከዚህ ቀደም የነበረውን የብድር አስተዳደራቸውን የሚያዘመንና በኢኮኖሚው ውስጥ ተገቢውን ሚና እንዲወጡ የሚያግዝ መሆኑ ታወቋል፡፡
የእዳና ሀብት አስተዳደር ኮርፖሬሽን በጥር ወር 2013 ዓ.ም በሚኒስትሮች ምክር ቤት እንዲቋቋም የተወሰነ መሆኑ የሚታወስ ሲሆን ተጠሪነቱም ለገንዘብ ሚኒስቴር ነው፡፡