የጀርመን የኢኮኖሚ ትብብርና ልማት ሚኒስቴር ከፍተኛ የልኡካን ቡድን ከገንዘብ ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራራ ጋር በሁለትዮሽ የኢኮኖሚ ትብብር ላይ መከረ

March 24, 2022

መጋቢት 15/ 2014 ዓ.ም - በምስራቅ አፍሪካ የስራ ጉብኝት በማድርግ ላይ የሚገኘው  የጀርመን የኢኮኖሚ ትብብርና ልማት ሚኒስቴር ከፍተኛ የልኡካን ቡድን ከገንዘብ ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች ጋር የሁለቱ ሀገራት ኢኮኖሚያዊ ትብብርና ልማት ድጋፍ በሚጠናከርበት ሁኔታ ላይ በገንዘብ ሚኒስቴር የመሰብሰቢያ አዳራሽ ፍሪያማ ምክክር አድርገዋል፡፡

የጀርመን መንግስት ከኢትዮጵያ ጋር ባለው የረጅም ጊዜ የሁለትዮሽ የኢኮኖሚ ትብብር ለኢትዮጵያ የሚሰጠውን የልማት ድጋፍ አጠናክሮ በሚቀጥልበት ሁኔታ ላይ እንዲሁም የኢትዮጵያ ዘላቂ እድገትና ልማት በሚረጋገጥበት አግባብ ላይ ሰፋ ያለ ውይይት አድርገዋል፡፡

በጀርመን የኢኮኖሚ ትብብርና ልማት ሚኒስቴር የምስራቅ አፍሪካ ሀላፊ በሚስተር ቮን ኢሰን ማርከስ   የተመራ ቡድን ከገንዘብ ሚኒስቴር የኢኮኖሚ ትብብር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ከክብርት ወ/ሮ ሰመሬታ ሰዋሰውና ከሚኒስቴሩ ከፍተኛ ሀላፊዎች ጋር በተወያዩበት ወቅት ክብርት ሚኒስትር ዴኤታዋ ስለኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ  ማለትም ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ማሻሻያ ረገድ፣ በግብርና ልማት፣ በጦርነት የተጎዱ ዜጎችን መልሶ ለመቋቋም ስለሚደረገው ጥረት፣ የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ውጤታማ ለማድረግ ስለሚደረገው ጥረት፣ አንዳንድ የመንግስት ይዞታዎችን ለውጭ ኢንቨስተሮች ክፍት የማድረግ አንቅስቃሴና የግሉ ዘርፍን በኢኮኖሚው ውስጥ ወሳኝ ሚና እንዲጫወት ስለሚደረገው ጥረት እንዲሁም ዘላቂ ሰላምና ልማት እውን እንዲሆን ለማስቻል የብሄራዊ ምክር ሂደት መጀመሩን በተመለከተ  ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሁነኛ የልማት አጋር የሆነችው ጀርመን የኢትዮጵያን ልማት ስትደግፍ የቆየች መሆኗን ክብርት ወ/ሮ ሰመሬታ ጠቀሰው ኢትዮጵያ ከልማት አጋሮች ዘርፈ ብዙ ድጋፎችን የምትፈልግ መሆኗንና ጀርመንም በተለይ አንገብጋቢ በሆኑት በስራ ፈጠራ፣ በድህነት ቅነሳ፣ በግብርና ልማት፣ በሴቶችና ወጣቶች የስራ ፈጠራ እንዲሁም በጦርነት የተጎዱ ወገኖች መልሶ በማቋቋም ድጋፏን እንድትሰጥ ጠይቀዋል፡፡

ሚስተር ቮን ኢሰን ማርከስ በበኩላቸው እንደገለጹት የጀርመን መንገስት የኢትዮጵያ መንግሰት የቅድሚያ ትኩረት በሰጣቸው በስራ ፈጠራ፣ በግብርና፣ የግሉን ዘርፍ በማጠናከርና በግጭት የተጎዱትን ዜጎች መልሶ በመቋቋም ዘርፍ ድጋፍ ማድረግ እንደሚፈልግ አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከግጭትና ያለመረጋጋ ወጥታ ልማትና እድገቷ እንዲረጋጋጥ ጀርመን የበኩሏን አስተዋጽኦ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗንና የኢትዮጵያ መንግስትም ዘላቂ ሰላም አንዲሰፍን ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

በውይይቱ በኢትጵዮያ የጀርመን አምባሳደር ሚስተር ስቴፓን አውር እንዲሁም በኤምባሲው የልማት ትብብ ሀላፊ ሚስስ ላውራ ስሚትስ የተገኙ ሲሆን በጀርመንና በኢትዮጵያ መንግስታት የሚካሄደው የልማት ትብብር ወይይትና ተባብሮ የመስራት ሂደት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡

966 Views