የገንዘብ ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም እና የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ውይይት ተካሄደ
By: Yonas M. | Published: Aug. 18, 2025
ነሐሴ 12 / 2017 ዓ.ም - በውይይቱ ላይ የተገኙት የገንዘብ ሚንስትር ክቡር አቶ አህመድ ሽዴ እንደገለጹት በ2017 በጀት ዓመት በተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም መሰረት የፊስካልና የገንዘብ ፖሊሲ ማሻሻያዎች ተግባራዊ ተደርገዋል። በዚህም መሰረት ከታክስ የተገኘው ገቢ ካለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር በከፍተኛ ሁኔታ አድጓል ብልዋል፡፡
መንግስት የበጀት ጉድለትን ለማሟላት ከብሔራዊ ባንክ ብድር እንዳይወሰድ ተደረጓል፣ ጉድለቱም የዋጋ ግሽበትን ከማያባብሱ የፋይናንስ ምንጮች ማለትም ከትሬዠሪ ቢል እና ቦንድ ብድር ተወስዶ እንዲሸፈን ተደርጓል ሲሉ አቶ አህመድ ገለጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት እና አጋር መንግስታት ጋር በተደረገ ድርድር (እ.ኤ.አ ከ2023 - 2024) የዕዳ ክፍያ ጊዜ እንዲራዘም መደረጉን ጠቁመዋል፡፡
በሌላ በኩል የመንግስት ዲጂታል ስርዓት ድርሻን በማሳደግ ረገድ 169 ባለበጀት መ/ቤቶች በ2017 ዓ.ም የኤሌክትሮኒክስ ክፍያ እንደፈጸሙ በውይይቱ ላይ ተጠቀሷል፡፡
በቀጣይ የ2018 በጀት ዓመት የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲና የኢኮኖሚ ማሻሻያን እና የየዘርፉን እቅድ መነሻ በማድረግ የሀገር ውስጥ ገቢን የተሻሻለ በማድረግ የታክስ ገቢ ከጠቅላላው የሀገር ውስጥ ምርት ያለውን ድርሻ ከፍ እንዲል ይደረጋል ብለዋል፡፡
የውጭ አጋርነትን በማጠናከር የውጪ የልማት ሀብት አቅርቦት ለማሳደግ ከነባርና አዳዲስ ምንጮች ተጨማሪ የውጭ ሀብት እንዲገኝና ወደ ሀገር ውስጥ እንዲፈስ ይደረጋሉ ሲሉ ጨምረው ገልፀዋል፡፡