የገንዘብ ሚኒስቴርና የተጠሪ ተቋማት አመራሮችና ሰራተኞች በአንድ ጀንበር 600 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል መርሀ ግብር አረንጓዴ አሻራቸውን አኖሩ
Aug. 23, 2024ነሐሴ 17 / 2016 ዓ.ም - የገንዘብ ሚኒስቴርና የተጠሪ ተቋማት አመራሮችና ሰራተኞች በሀገር አቀፍ ደረጃ በአንድ ጀንበር 600 ሚሊዮን ችግኞችን የመትከል መርሀ ግብር ላይ በመሳተፍ በአዲስ አበባ ከተማ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ሜቄዶንያ የበጎ አድራጎት ማህበር አካባቢ አራንጓዴ አሻራቸውን አኖሩ፡፡
የገንዘብ ሚኒስትር ክቡር አቶ አህመድ ሺዴ አረንጓዴ አሻራቸውን ካኖሩ በኋላ እንደገለጹት ላለፉት ተከታታይ አመታት በተካሄደው ሀገር አቀፍ አረንጓዴ አሻራ የማኖር መርሀግብር የላቀ ሀገራዊ ንቅናቄና ህዝባዊ ተሳትፎ የታየበት መሆኑን ጠቁመው በዛሬው ዕለት በመላው ኢትዮጵያ በሚካሄደው በአንድ ጀንበር 600 ሚሊዮን ችግኞች የመትከል መርሀ ግብር ላይ የገንዘብ ሚኒስቴርና የተጠሪ ተቋማት አመራሮችና ሰራተኞች የአረንጓዴ አሻራ የማኖር አካል በመሆናችን ደስታ ይሰማናል ብለዋል፡፡
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ኢዮብ ተካልኝ በበኩላቸው አረንጓዴ አሻራ የማኖር መርሀ ግብር በሀገር ደረጃ ሁሉም ዜጎች የሚሳተፉበት ሀገር አቀፍ ንቅናቄ መሆኑን ጠቅሰው ችግኞችን በመትከል የደን ሽፋንን ማስፋት ምርትና ምረታማነትን በማሳደግ ለሀገር ልማትና ኢኮኖሚያዊ እድገት የላቀ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል፡፡
የገንዘብ ሚኒስቴር የኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ ሰመሪታ ሰዋሰውም በስፍራው ተገኝተው አረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል፡፡