የገንዘብ ሚኒስቴርና የተጠሪ ተቋማት የ2013 በጀት ዓመት አፈጻጸምና የ2014 በጀት ዕቅድ ወይይት አካሄደ
July 30, 2021
ሐምሌ 23 2013 ዓ.ም ፡- የገንዘብ ሚንስትር ክቡር አቶ አህመድ ሽዴ ውይይቱን የመሩት ሲሆን በ2013 በጀት አመት በመስሪያ ቤቱ ለተመዘገበው የስራ አፈጻጸምና ውጤት መላውን ሰራተኛ አመስግነው በቀጣዩም የ2014 በጀት አመትም ወጤት እንዲመዘገብ ተግቶ መስራት አንደሚገባ አመልከተዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ የኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተግባራዊ ለማድረግ የተለያዩ ፖሊሲዎችን በመቅረዕና በማስፈፀም የተደረገው ጥረት የሚያበረታታ መሆኑንም ገልጸው የኮቪድ ወረርሽኝ ያስከተለውን ተጽእኖ በመቋቋም የማክሮ ኢኮኖሚውን ለማረጋጋትና የኢኮኖሚ እድገቱን ለማስቀጠል የተደረገውም ጥረት ተስፋ ሰጪ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
በ2013 በጀት አመት ከማዕከላዊ ግምጃ ቤት ከተፈቀደው በጀት ብር 448.5 ቢሊዮን ውስጥ ብር 406.8 ቢሊዮን (90 በመቶ) ክፍያ እንዲተላለፍ መደረጉ በውይይቱ ወቅት ተገልጽዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ ከልማት አጋሮች በእርዳታና ብድር በድምሩ ብር 4.3 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ ብር 3.9 ቢሊዮን ዶላር (90.7 በመቶ) ተገኝቷል፡፡ ፍሰትን በተመለከተ ደግም ብር 3.9 ቢሊዮን ዶላር ታቅዶ አፈጻጸሙ ብር 3.1 ቢሊዮን (79.5 በመቶ) መፈሰስ እንደቻለ ተገልጽዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ ካጋጠሙ ዋናዋና ችግሮች መካከል ከአንዳንድ የልማት አጋሮች በበጀት ድጋፍ መልክ እንደሚፈስ የታቀደው የእርዳታና ብድር መዘግየት፣ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት የፕሮጀክቶችን አፈጻጸም በመስክ ግምገማ ለመከታተል አለመቻሉ እና የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ችግር የመሳሰሉት ተጠቅሰዋል፡፡
በ2014 በጀት ዓመት የመንግስት የፋይናንስ አስተዳደርን ለመሻሻል፣ የፕሮግራም በጀት አሰራርን ወደ ሁለት ክልሎችና አንድ የከተማ አስተዳደር ማውረድ፣ በተመረጡ ሰባት የፌዴራል መስሪያ ቤቶች ላይ የኤሌክትሮኒክስ የመንግስት ግዥ (e-GP) የሙከራ ትግበራ ማከናወን፣ በ60 የፌዴራል ባለበጀት መስሪያ ቤቶች ላይ የተቀናጀ የፋይናንስ አስተዳደር መረጃ ስርዓትን (IFMIS) መዘርጋት፣ በ188 ተቋማት ስጋትን መሰረት ያደረገ የኦዲት ግምገማ ማድረግ፣ በተለያዩ 40 ተቋማት የክዋኔ ኦዲት የዳሰሳ ጥናት ማድረግ፣ 40 በመቶ የሚሆነውን የኢትዮ ቴሌኮም ድርሻ ሽያጭ ማጠናቀቅ፣ አራት የስኳር ፋብሪካዎችን መሸጥ እና የሚኒስቴሩን አደረጃጀት ፈትሾ እንደገና የማስተካከል የማስተካከል እቅዶች ተይዘዋል፡፡
በውይይቱ መ የገንዘብ ሚኒስቴር ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና የተጠሪ ተቋማት ማለትም የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ፣ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ፣ የመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት እንዲሁም የኢትዮጵያ ሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ የስራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል፡፡